ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶጋን ከሩሲያ አቻቸው ቪላድሚር ፑቲን ጋር ለመወያየት ቀጠሮ መያዛቸው ተገለጸ

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲብ ጣይብ ኤርዶን ወደ ሩሲያ ተጉዘው ከፕሬዝዳንት ቪላድሚር ፑቲን ጋር ለመወያየት ቀጠሮ መያዛቸው ተገለጸ፡፡

መሪዎቹ ቱርክ በሶሪያ ላይ የሰነዘረችውን ወታደራዊ ዘመቻ በሚመለከት እንደሚመክሩ የተገለጸ ሲሆን፣ የሶሪያው ፕሬዝዳንት በሽር አላሳድ ለሶስትዮሽ ውይይት የመሪዎቹን ስብሰባ ሊቀላቀሉ ይችላሉ የሚለው ቅድመ ግምት ውድቅ መሆኑም ታውቋል፡፡

ቱርክ በሰሜን ሶሪያ የሰነዘረችውን ወታደራዊ ጥቃት ተከትሎ የሶሪያ መንግስት ወታደሮቹን ከኩርድ አማጺያን ጋር እንዲቀላቀሉ ወደ ድንበር ከተማ ማሰማራቱ ይታወሳል፡፡

ቱርክ በሶሪያ ላይ የሰነዘረችው ጥቃት በተለያዩ ሀገራት ውግዘት እየደረሰበት ቢገኝም እሷ ግን በዘመቻዋ ቀጥላለች፡፡ ጥቃቱም ስምንተኛ ቀኑን ቢያስቆጥርም አንካራ ወደ ኋላ የምትመለሰው አሸባሪዎች ከተሰገሰጉባት የሶሪያ ኩርድ ግዛት ማጽዳት ከቻልን ብቻ ነው ሲሉም ኤርዶጋን ማስጠንቀቂያ አዘል መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

የጥቃቱ አላማ በቱርክና በሶሪያ ድንበር አቅራቢያዎች ላይ በኩርድ አማጺያን የሚመራውን ሀይል ከድንበር አቅራቢያው ወደ ኋላ እንዲያፈገፍግ በማድረግ ለሶሪያውያን ከስደት ተመላሾች ደህንነቱ የተጠበቀ ስፍራን ማመቻቸት እንደሆነ ከቱርክ በኩል እየተገለጸ ይገኛል፡፡

ፕሬዝዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶጋን ወደ ሩሲያ ተጉዘው ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ለመወያየት ቀጠሮ መያዛቸውን ትናንት የወጡ መረጃዎች እየጠቆሙ ሲሆን፣ ሩሲያ የሶሪያ ዋነኛ ወታደራዊ ድጋፍ ሰጭ ሀገር እንደሆነችም ይታወቃል፡፡

መሪዎቹ ቱርክ በሶሪያ ላይ የሰነዘረችውን ወታደራዊ ዘመቻ በሚመለከት እንደሚመክሩ የቱርክ ፕሬዘዳንት ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡ የመሪዎቹ ውይይት በሩሲያዋ ሶቺ ከተማ የፊታችን ጥቅምት 11 እንደሚካሄድ ከቱርክ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የወጣው መረጃ ይጠቁማል፡፡

የመሪዎቹ የውይይቱ የትኩረት አቅጣጫን በተመለከተ መረጃው ዝርዝር ጉዳዮችን ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡

የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ የሁለቱን መሪዎች ስብሰባ የሶሪያው ፕሬዝዳንት በሽር አላሳድ ለሶስትዮሽ ውይይት ሊቀላቀሉ ይችላሉ የሚለውን ቅድመ ግምት ውድቅ አድርገውታል ሲል አልጀዚራ ዘግቧል፡፡