ቱርክ ሶሪያ ላይ የከፈተችውን ጥቃት ለማቋረጥ ተስማማች

ቱርክ በሰሜን ሶሪያ የከፈተችውን ጥቃት በኩርዶች የሚመራው ጦር እስኪወጣ ድረስ ለማቋረጥ ተስማማች።

ስምምነቱ የተደረሰው የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ እና የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን በአንካራ ተገናኝተው ከመከሩ በኋላ ነው ተብሏል።

ሁሉም ውጊያዎች ለቀጣይ አምስት ቀናት የሚቋረጡ ሲሆን፣ አሜሪካ የኩርድ ወታደሮች ስፍራውን ለቅቀው እንዲወጡ እንደምታደርግ ማይክ ፔንስ ተናግረዋል።

ሁለቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ይህንን ይስማሙ እንጂ በዚህ ጉዳይ ያላቸው የኩርዶች አቋም አልታወቀም።

ኮማንደር ማዝሎኡም ኮባኒ እንደሚሉት ከሆነ በኩርዶች የሚመራው ጦር ጠንካራ ውጊያ በሚደረግባቸው የድንበር ከተሞች ሆኖ ስምምነቱን ሲመለከት ነበር።

እነዚህ ውጊያ የሚደረግባቸው ከተሞች ራስ አል አዪን እና ጣል አባይድ የሚሰኙ ሲሆን፣ "የሌሎቹን አካባቢዎች ዕጣ ፈንታ አልተነጋገርንም" ብለዋል።

መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው በሶሪያ ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ የሚከታተል አንድ ቡድን እንዳለው፤ ምንም እንኳ ተኩስ ለማቆም ስምምነት ላይ ቢደረስም በራስ አል አዪ አሁንም ተኩስ እንደቀጠለ ነው።

ባለፉት ስምንት ቀናት በአካባቢው በነበረው ውጊያ 72 ንፁሃን ዜጎች የሞቱ ሲሆን 300 ሺህ ሰዎች ተፈናቅለዋል።

ቱርክ ባለፈው ሳምንት በድንበር አካባቢ ጥቃት የከፈተችው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሶሪያና በቱርክ ድንበር አካባቢ ሰፍሮ የነበረውን ሠራዊታቸውን እንዲወጣ ካደረጉ በኋላ ነው።

ቱርክ ለጥቃቱ ምክንያት አድርጋ የምታቀርበው የኩርድ ሚሊሻ ቡድኖችን ከስፍራው ማስወጣትን ሲሆን እነዚህ ቡድኖች በቱርክ በኩል እንደ አሸባሪ ነው የሚታዩት።

ቱርክ በዚህ የድንበር አካባቢ 2 ሚሊዮን ስደተኞችን ለማስፈር ያቀደች ቢሆንም፤ ይህንን እርምጃ የሚተቹ ወገኖች ግን በአካበቢው የኩርዶችን ዘር ለማጥፋት የሚወሰድ ርምጃ ሲሉ ኮንነውታል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ አጋር የነበሩትን የሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ጦርን በመተዋቸው እየተወቀሱ ይገኛሉ።

ይህ ቡድን አሜሪካ ከ አይ ኤስ ጋር ባደረገችው ጦርነት ከጎኗ ተሰልፎ ተዋግቷል።

ረቡዕ እለት ትራምፕ ኩርዶችን "መልዓክ አይደሉም" በማለት የድንበር አካባቢውን ደግሞ "የእኛ ድንበር አይደለም፤ የሕይወት መስዋዕትነት መክፈል የለብንም" ሲሉ ተደምጠዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቱርክ ተኩስ ለማቆም መስማማቷን ምክትል ፕሬዝዳንታቸው ከቱርክ ይፋ ከማድረጋቸው ቀደም ብሎ ትዊተራቸው ላይ "የሚሊዮኖች ሕይወት ይድናል" በማለት ጽፈዋል።

ማይክ ፔንስም ስምምነቱን በገለፁበት ወቅት የዶናልድ ትራምፕን "ጠንካራ አመራር" እውቅና ሰጥተዋል።

ማይክ ፔንስ ከኤርዶጋን ጋር ከመገናኘታቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ትራምፕ ለቱርክ አቻቸው "ድርቅ አትበል፤ ሞኝ አትሁን" የሚል ደብዳቤ ጽፈውላቸው ነበር።

ስምምነቱ ከተደረሰ በኋላም "እንዴት ያለ መሪ ነው፤ ትክክለኛውን ነገር ያደረገ" ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡