በኢንዶኔዢያ በጀልባ መስጠም ምክንያት 31 ሰዎች ሞቱ

በኢንዶኔዢያ ሲላዊስ ደሴት አንድ ጀልባ ሰጥማ 31 ሰዎች የሞቱ ሲሆን 3ቱ እስካሁን አልተገኙም ፡፡

ሀገሪቱ በሁለት ሳምንታት ውስጥ ተመሳሳይ አደጋ ስታስተናግድ ያሁኑ ለአራተኛ ጊዜ የተከሰተ ነው፡፡

በተለያዩ የተፈጥሮ መስህቦች የምትታወቀው እና በዓለም ትልቅ ከሚባሉ ደሴቶች መካከል የበርካቶቹ ባለቤት የሆነችው እስያዊቷ ሃገር ኢንዶኔዥያ በጥንቃቄ ጉድለት ምክንያት በርካታ አደጋዎችን እያስተናገደች ትገኛለች፡፡

በተለይ የጀልባዎች መስጠም አዲሷ ያልሆነው ኢንዶኔዢያ የአደጋውን ያክል ግን ለደህንነት ትኩረት አልሰጠችም፡፡

ከሁለት ሳምንታት በፊት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሙስሊሞች የረመዳንን በዓል ለማክበር ወደቤታቸው ሲመለሱ በአንድ ጀልባ ተሳፍረው የነበሩት ጀልባዋ ከምትችለው ሶስት እጥፍ በዝተው እንደነበሩና በዚሁም አብዛኞቹ ጀልባዎች የሰጠሙ ሲሆን 200 የሚሆኑ ሰዎች የገቡበት አልታወቀም ሲል አልጀዚራ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ሮይተርስ በበኩሉ በጀልባዎቹ መስጠም ምክንያት 200 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል ብሏል፡፡

በወቅቱ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆኮ ዊደዶ ተመሳሳይ ችግር እንደማይከሰት እና በትራንስፖርቱ ላይ ያለው የደህንነት ክፍተት እንዲታረም አዘዋል፡፡

‹‹እንደዚህ አይነቱ እልቂት ድጋሚ እንዳይከሰት ጥንቃቄ እንድታደርጉ እጠይቃለሁ፡፡ እያንዳንዱ የጥንቃቄ ሂደት ዋጋ ተሰጥቶት እንዲሰራ ትራንስፖረርት ሚኒስቴርን አዝዣለሁ፡፡››

ፕሬዝዳንቱ ይህን ይበሉ እንጂ የትዕዛዛቸው ተግባራዊነት ከሁለት ሳምንታት የዘለለ አልነበረም፡፡

እሳቸው በተናገሩ ልክ በሁለተኛው ሳምንት በሃገሪቱ ሲላዊስ ደሴት አንድ ጀልባ ሰጥማ ይህ ዜና እስኪጠናቀር ቢያንስ 31 ሰዎች የሞቱ ሲሆን የሶስቱ እስካሁን አልተገኘም የተባለው፡፡

የሃገሪቱ ብሔራዊ ፍለጋ እና የነፍስ አድን ድርጅት እንዳለው ጀልባዋ ይዛቸው ከነበሩት 164 ሰዎች መካከል 130ዎቹ በህይወት የተረፉ ሲሆን ሶስቱ እስካሁን አልተገኙም፡፡ (ሮይተርስ እና አልጀዚራ)