አሜሪካ ስደተኞችን ፍርድ ቤት ሳታቀርብ ወደመጡበት አገር መመለስ ልትጀምር ነው

አሜሪካ ስደተኞችን ፍርድ ቤት ሳታቀርብ ወደመጡበት አገር መመለስ ልትጀምር ነው
የአሜሪካ መንግሥት የስደተኞች ፍርድ ቤትን አልፎ ስደተኞችን በፍጥነት ወደ መጡበት አገር ለመመለስ የሚያስችል መመሪያ ማውጣቱ ተገለጸ።
በአዲሱ ደንብ መሰረት ማንኛውም ማስረጃ የሌለው ስደተኛና በተከታታይ ለሁለት ዓመት አሜሪካ ውስጥ እንደነበር ማረጋገጥ ያልቻለ ግለሰብ ወደ መጣበት አገር እንዲመለስ ይደረጋል።
ፖሊሲው ዛሬ ይፋ ተደርጎ በሁሉም የአሜሪካ ግዛቶች በአፋጣኝ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል ተብሏል።
አሜሪካን ሲቪል ሊበርቲስ ዩኒየን የተባለ የመብት ተሟጋች ቡድን ፖሊሲውን በመቃወም ፍርድ ቤት ወስዶ ለመሟገት ማሰቡን ተናግሯል።
የአሜሪካ የስደተኞች ፖሊሲ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥብቅ እየሆነ እየመጣ መሆኑን የሚያስረዱ አካላት አገሪቱ በደቡብ በኩል ከሜክሲኮ ጋር በሚያዋስናት አካባቢ የምታደርገውን በመጥቀስ የጉዳዩን አሳሳቢነት ያብራራሉ።
የአገር ውስጥ ደህነንነት መሥሪያ ቤቱ ተጠባባቂ ዋና ጸሀፊ ኬቨን ማክአሌናን፤ "ይህ ለውጥ በድንበር አካባቢ ያለብንን ጫናና የአቅም ጉዳይ ያነሳልናል" ሲሉ አሞካሽተውታል።
አክለውም "ቀጣይነት ላለው የስደተኞች ቀውስ ምላሽ የሚሰጥ" ብለውታል።
የአሜሪካ የስደተኞች ጉዳይ ላይ ትንታኔ የሚሰጡ ባለሙያዎች በበኩላቸው, ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለ2020 ምርጫ ስደተኞችን መቆጣጠርን ቁልፍ ጉዳይ ለማድረግ መወሰናቸውን ያሳያል ይላሉ።
ከዚህ ቀደም ሰዎች ወደ መጡበት አገር ወዲያውኑ እንዲመለሱ የሚደረገው ከአሜሪካ ድንበር በ160 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ውስጥ ሲገኙና አሜሪካ ከገቡ ከሁለት ሳምንት በታች የሆናቸው ከሆኑ ብቻ ነበር።
በአገሪቱ የትኛውም አካባቢ የሚገኙ ስደተኞች ወይንም ከሁለት ሳምንት በላይ የሆናቸው ግለሰቦች ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤት ተመርቶ ሕጋዊ ውክልና የማግኘት መብታቸው ተጠብቆ እንዲቆዩ ይደረግ ነበር።
አዲሱ ሕግ ግን ማንኛውም ስደተኛ በየትኛውም የአገሪቱ ስፍራ ቢገኝ በቁጥጥር ስር ከዋለ ያለ ጠበቃ ውክልና ወደመጣበት እንዲመለስ ይደረጋል። 
ጥገኝነት ለመጠየቅ የሚያበቃ ምክንያት ያላቸው፤ የጥገኝነት ጉዳዮችን የሚከታተለውን ባለሙያ የማናገር መብት አላቸው ይላል።
ሰኞ ዕለት ፖሊሲው በተዋወቀ በሰአታት ውስጥ የመብት ተሟጋች ድርጅቱ አሜሪካን ሲቪል ሊብረቲስ ዩኒየን ጉዳዩን ፍርድ ቤት በመውሰድ ለመሞገት ማሰቡን አስታውቋል።
"ይህንን የትራምፕ እቅድ ለማስቆም በፍጥነት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደን ክስ እንመሰርታለን" ሲሉ በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።
"በአሜሪካ ለረዥም ጊዜ የቆዩ ስደተኞች በትራፊክ ደህንነት ጥሰት ፍርድ ቤት ከሚቀርቡ ሰዎች ያነሰ በፍርድ ቤት የመከራከር እድል አላቸው" ሲሉም ምሬታቸውን ገልፀዋል።
በሲቪልና ሰብዓዊ መብቶችን ጉባኤ ፕሬዝዳንት የሆኑት ቫኒታ ጉፕታ፣ የፕሬዝዳንት ትራምፕን እቅድ የስደተኞች ጉዳይ የሚያየውን ተቋም "ወረቀታችሁን አሳዩን ወደሚል ፈርጣማ ኃይል" እየቀየሩት ነው ብለዋል።
የሕግ ባለሙያ የሆኑት ጃኪ ስቲቨንስ በበኩላቸው፣ ወደመጣችሁበት አገር ተብለው ከሚመለሱ ሰዎች መካከል የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው እንደሚገኙበት ገልፀዋል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)