ሳዑዲ አረቢያ ሴቶች ያለማንም ረዳት እንዲጓዙ ፈቀደች

ሳዑዲ አረቢያ ሴቶች ያለ ወንዶች ረዳትነትና ፈቃድ ፓስፖርት እንዲያወጡና ከአገር ውጭ እንዲጓዙ ፈቀደች።

ባለፈው አርብ ይፋ የተደረገው አዲሱ ሕግ፤ እድሜያቸው ከ21 ዓመት በላይ የሆናቸው ሴቶች ያለወንድ ረዳቶቻቸው ወይም አጋሮቻቸው ፈቃድ ፓስፖርት ለማውጣት ማመልከት እንዲችሉ ይፈቅዳል።

ማንኛውም አዋቂ የሆነ ሰው ፓስፖርት ኖሮት ከአንድ አገር ወደሌላ እንዲጓዝ የሚያደርገው ሕግም ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ መብት ረገድ ሴቶችን ከወንዶች እኩል አድርጓቸዋል።

ሕጉ ጨምሮ እንዳስቀመጠው ሴቶች የውልደትን፣ ጋብቻንና ፍቺን ማስመዝገብ እንዲችሉም ተፈቅዷል።

ከዚህም በተጨማሪም የሴቶችን የሥራ እድል የሚመለከተውን የሥራ ቅጥር ሕግ ተመልክቷል። በዚህ ሕግ ማንኛውም የአገሪቱ ዜጋ ያለምንም ልዩነት፤ ያለ ፆታ፣ የአካል ጉዳት ወይም እድሜ መድልዎ እኩል የመሥራት መብት እንዳላቸው አትቷል።

እስካሁን ድረስ የሳዑዲ ሴቶች ፓስፖርት ለማግኘትና ወደ ሌላ አገር ጉዞ ለማድረግ ከትዳር አጋራቸው፣ ከአባታቸው አሊያም ከሌላ ወንድ ዘመዳቸው ፈቃድ ማግኘት ይጠበቅባቸው ነበር።

ከዚህ ቀደም የሳዑዲ አረቢያው ልዑል ሞሐመድ ቢን ሰልማን ሴቶች ማሽከርከር እንዳይችሉ የሚከለክለውን ሕግ ማንሳታቸው ይታወሳል።

ይህም በአገሪቷ ለሴቶች እድሎች እየተከፈቱ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው ተብሏል።

ልዑል ሞሐመድ ቢን ሰልማን የሴቶችን በሥራ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ከነበረው 22 በመቶ ወደ 30 በመቶ ከፍ በማድረግ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በ2030 ለማሳደግ ዓላማ ይዘው እየሠሩ መሆናቸውን ከሦስት ዓመታት በፊት አስታውቀው ነበር።

ይሁን እንጂ በርካታ ከፍተኛ እውቅና ያላቸው ሴቶች የሚደርስባቸውን የፆታ መድልዎ ምክንያት በማድረግ በካናዳና በተለያዩ አገራት ጥገኝነት ይጠይቃሉ።

ባለፈው ጥር ወር የ18 ዓመቷ ራሃፍ መሀመድ አልቁኑን በካናዳ ጥገኝነት ተሰጥቷታል። ራሃፍ ከሳዑዲ አረቢያ የተሰደደች ሲሆን ወደ አውስትራሊያ ለመግባት ሞክራ ነበር። በመጨረሻም በታይላንድ ባንኮክ አየር ማረፊያ ሆቴል ተይዛ ዓለም አቀፍ እርዳታ እንዲደረግላት ጠይቃለች።

ይህች ሴት በአገሯ ላይ እንደሁለተኛ ዜጋ ተቆጥራላች ሲሉ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ቅሬታቸውን ያሰሙ ነበር። (ምንጭ፡- ቢቢሲ)