የዓለምን ሙቀት መጨመር ለመግታት የአስተራረስ እና የአመጋገብ ዘዬ ሊለወጥ እንደሚገባ ተገለጸ

የዓለምን ሙቀት መጨመር ለመግታት የአስተራረስ እና የአመጋገብ ዘዬ ሊለወጥ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

የሙቀት መጨመርን ወይም የምግብ ዋስትና፣ ጤና እና ብዝሀ ሕይወት ችግርን ለመግታት የዓለም ሕዝብ የመሬት አጠቃቀም፣ አመራረት እና አመጋገብ ላይ ለውጥ ማምጣት አለበት ነው የተባለው።

የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ቦርድ ዛሬ ይፋ ባደረገው ሪፖርት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የመጣው የሕዝብ ቁጥር እና የምግብ ፍጆታ አጠቃቀም በመሬት እና ውሃ አጠቃቀም ላይ ያልተጠበቀ ተፅዕኖ አሳድሯል ብሏል።

የአመጋገብ ሥርዓት ለውጥ ማድረግ፣ ተክሎችን መሠረት ያደረጉ እና ሚዛናዊ የሆነ ከእንስሳት ተዋጽኦ የተገኙ ምግቦችን መጠቀም እ.አ.አ በ2050 ላይ በሚሊየኖች የሚቆጠር መሬት ነፃ እንዲሆን ብሎም በየዓመቱ ከ0.7 እስከ 8.0 ጊጋ ቶን የሚደርስ በካይ ጋዝ ማስቀረት ይቻላል ብሏል።

ነገር ግን የተጠቀሱትን ተግባራት ከማድረግ መዘግየት በተወሰኑ ሥነ ምህዳሮች ላይ የማይካካስ ተፅዕኖ በማሳደር የዓለም ሙቀት መጨመርን ያባብሳል ሲል አትቷል።

የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ቦርድ ይህንኑ ሪፖርት ለማጠናቀቅ እና በያዝነው የፈረንጆች 2019 መጨረሻ አካባቢ በቺሊ ለሚካሄደው የዓለም ሙቀት መጨመር የተመለከተ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ግብዓት ለመስጠት በያዝነው ሳምንት ውስጥ ጄኔቫ ውስጥ ይገናኛል። (ምንጭ:-ሮይተርስ)