በካቡል ከተማ አንድ ሠርግ ላይ የፈነዳ ቦንብ 63 ሰዎችን ሲገድል 180 ሰዎችን አቁስሏል

በአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል አንድ ሠርግ ላይ የፈነዳ ቦንብ 63 ሰዎችን ሲገድል 180 ሰዎችን አቁስሏል፡፡

የዓይን እማኞች አንድ አጥፍቶ ጠፊ ቦንቡን ተሸክሞ መጥቶ እንዳፈነዳው የተናገሩት፡፡

ቦንቡ የፈነዳው ቅዳሜ ምሽት 4፡40 ገደማ ሲሆን ሥፍራው ደግሞ የሺያ ሙስሊሞች የሚያዘውትሩት የካቡል ምዕራባዊ ክፍል ነው ተብሏል።

ታሊባን 'እኔ እጄ የበለትም' ሲል አስተባብሏል። እስካሁን ለጥፋቱ ኃላፊነት የወሰደ ቡድን የለም። ራሳቸውን ከሱኒ ሙስሊሞች ጋር የሚያቆራኙት ታሊባን እና አይ ኤስ ከዚህ በፊት የሺያ ሙስሊሞች ላይ ጥቃት መፈፀማቸው ይታወሳል።

የአፍጋኒስታን ሃገር ውስጥ ሚኒስትር አደጋው ከደረሰ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የሟቾችን እና የተጎጂዎችን ቁጥር ይፋ አድርገዋል።

ወንዶች እና ሴቶች ለየብቻ ሆነው የሚስተናገዱበት የአፍጋኒስታን የሠርግ ሥነ-ሥርዓት በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ይታደሙበታል።

'አጋጣሚ ሆኖ ቦንቡ ሲፈነዳ እኔ ከሴቶች ጎራ ነበርኩ' የሚለው ሞሐመድ ፋርሃግ 'ከፍንዳታው በኋላ ሰዎች ሁላ እግሬ አውጭኝ እያሉ ሲወጡ ተመልክቻለሁ' ሲሉ ኤኤፍፒ ለተሰኘው የዜና ወኪል ተናግሯል።

ከ10 ቀናት በፊት ካቡል ውስጥ በሚገኝ አንድ ፖሊስ ጣብያ የፈንዳ ቦንብ የ14 ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉ አይዘነጋም። ታሊባን ጥፋቱን የፈፀምኩት እኔ ነኝ ሲል ኃላፊነቱን ወስዷል።

ባለፈው አርብ ደግሞ የታሊባን አለቃ ወንድም የሆነው ሂባቱላህ አኩንደዛዳ መስጅድ ውስጥ ሳለ በተመጠደ ቦንብ ሕይወቱ አልፏል።

አፍጋኒስታን ውስጥ በርካታ ወታደሮች ያሏት አሜሪካ ከታሊባን ጋር ድርድር ውስጥ እንዳለች እና በጎ ጅማሬዎች እንደታዩ ዕለት አርብ ፕሬዝደንቷ ትራምፕ በትዊተር ገፃቸው ማወጃቸው አይዘነጋም። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)