ብራዚል የአማዞን ደን ቃጠሎን ለመከላከል የእሳት አደጋ ሰራተኞቿን  ወደ ስፍራው ላከች

ብራዚል የአማዞን ደንን ከሰደድ እሳት ቃጠሎ ለመታደግ ወደ ስፍራው ወታደራዊ ሀይሏንና የእሳት አደጋ ሰራተኞቿን  መላኳ ተገለፀ፡፡

የአማዞን ደን ያጋጠመውን ሰደድ እሳት ተከትሎ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አደጋው ዓለማቀፍ መቅሰፍት  ስለሆነ  ክስተቱ በቡድን ሰባት ስብሰባ ላይ መነጋገሪያችን ሊሆን ይገባል ከማለት በተጨማሪ በቲዊተር ገጻቸው ላይ "ቤታችን እየነደደ ነው" ሲሉ አስፍረዋል።

የብራዚሉ ርዕሰ ብሔር ጃይር ቦልሶናሮ የማክሮንን አስተያየት ጉዳዩን ፖለቲካዊ ገጽታ ማላበስ ነው ሲሉ ወርፈዋል።

ብራዚል በሌለችበት ሰባቱ የበለጸጉ ሀገራት በአማዞን ሰደድ እሳት ጉዳይ ስብሳባ ለማድረግ መሞከር ምዕራባዊያን አሁንም ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ አለመላቀቃቸውን የሚያሳይ ነው ሲሉም ፕሬዝዳን ቦልሶናሮ አክለዋል።

የብራዚሉን ፕሬዝዳንት አሰተያየት እንደዋዛ ያላዩትት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የብራዚሉ አቻቸው የሰደድ እሳቱን ለመቆጣጠር አስፈለጊውን እርምጃ የማይወስዱ ከሆነ የደቡብ አሜሪካ ሀገራት ከአውሮፓ ህብረት ጋር ከሃያ ዓመታት ድርድር በኋላ የተደረሰውን የንግድ ስምምነት ተግባራዊ እንዳይሆን አደርጋለሁ ብለዋል፡፡

ይህን የማክሮን አስተያየት ተከትሎ ብራዚል ዛሬ የእሳት ቃጠሎውን ለመቆጣጠር የእሳት አደጋ ሰራተኞችን ወደ ቦታው መላኳን አስታውቃለች፡፡

ብራዚል ይህንን ያደረገችው ከአውሮፓ ሀያላን ሀገሮች የመጣውን ተደጋጋሚ ጫና ተከትሎ እንደሆነም ነው የተነገረው፡፡

እናም ብራዚል የአማዞን ቃጠሎን ለመታደግ ወታደሮቿንና የእሳት አደጋ ሰራተኞቿን የአንድ ወር የዘመቻ ጊዜ ሰጥታቸዋለች፡፡

የአማዞን ጥቅጥቅ ደን ከፍተኛ የሆነ ኦክስጅን ለዓለም ከባቢ አየር እንደሚያበረክት ሲሆን፤ የዓለማችን ትልቁ ደን አማዞን ከ3 ሚሊየን በላይ የእንስሳትና እፅዋት ዝርያዎች እንዲሁም ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን በውስጡ አቅፎ ይዟል፡፡

አሁን ግን  አማዞን እየተቃጠለ ነው ብራዚሊያዊያን ደግሞ ጩኸታቸውን ወደ ፕሬዝዳንት ቦሎሶናሬ አድርገዋል ተብሏል፡፡

ብራዚል የአማዞን ደንን ከቃጠሎ ለመታደግ በምታደርገው ጥረት የአሜሪካ እና እስራኤልን ድጋፍም መጠየቋ የተነገረ ቢሆንም፤የዓለም መሪዎች የዓለም ሳምባ በመባል የሚታወቀውን የዓማዞን ደን  ለመታደግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከማድረግ ይልቅ ዝምታን መምረጣቸው አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

ዘገባው የቢቢሲ እና አልጀዚራ ነው፡፡