ቦይንግ በአውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ሰዎች ቤተሰቦች ካሳ ሊከፍል ነው

በቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ የሞቱ ሰዎች ቤተሰቦች ከቦይንግ ኩባንያ ለእያንድንዱ ሟች 144 ሺህ 500 ዶላር ሊከፈላቸው ነው።

በኢንዶኔዢያው ላየን ኤርና በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ላይ በደረሰው አደጋ ለሞቱት 346 ሰዎች ከቦይንግ የገንዘብ ድጋፍ ፈንድ ወጪ ተደርጎ ለአደጋዎቹ ሰለባ ቤተሰቦች እንዲከፈል 50 ሚሊዮን ዶላር ተመድቧል።

በሐምሌ ወር ቦይንግ ይፋ ያደረገው ቀሪ የ100 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ደግሞ ለትምህርትና ለልማት ፕሮግራሞች ይውላል ተብሏል።

ገንዘቡን የሚከፍለው አካል የይገባናል ጥያቄዎችን መቀበል የጀመረ ሲሆን፣ ጥያቄዎች ከፈረንጆቹ 2020 በፊት መቅረብ አለባቸው ተብሏል።

ኩባንያው ባወጣው መግለጫ ላይ የቦይንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዴኒስ ሙሊንበርግ፤ ገንዘብ ለመስጠት የተወጠነው ሃሳብ መጀመሩ በቦይንግ 737 ማክስ 8 አደጋዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቤተሰቦችን ለመርዳት ኩባንያው ለሚያደርገው ጥረት "ጠቃሚ እርምጃ" ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።

አደጋው ከደረሰባቸው አውሮፕላኖች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ 737 ማክስ አውሮፕላኖች በሙሉ ከባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ በመርማሪዎች የአውሮፕላኖቹ ደህንነት አስተማማኝነት እስኪረጋገጥ ድረስ ከበረራ ውጪ እንዲሆኑ ተደርጓል።

ቦይንግ ሐምሌ ወር ላይ በአደጋው ለሞቱት ሰዎች ቤተሰቦች ገንዘብ ለመስጠት እንዳሰበ ባሳወቀበት ጊዜ የአንዳንድ ቤተሰቦች ጠበቆች ከቦይንግ የቀረበው ገንዘብ በቂ እንዳልሆነ በመጥቀስ ውድቅ አድርገውት ነበር። በርካቶችም ኩባንያው ላይ በፍርድ ቤት ክስ ከፍተውበታል።

ቦይንግ ለአደጋዎቹ ሰለባ ቤተሰቦች ሊሰጥ ያዘጋጀውን ገንዘብ የሚከታተሉት የሕግ ባለሙያ ኬኔት ፋይንበርግ እንደተናገሩት፤ ቤተሰቦች ገንዘቡን ሲወስዱ በሙሉ ፈቃዳቸው ሲሆን፣ በኩባንያው ላይ የተናጠል ክስ ለመመስረት ያላቸውን መብት እንዲተዉ የማያስገድድ መሆኑን አመልክተዋል።

የሕግ ባለሙያው ለአደጋው ሰለባዎች የተዘጋጀን ገንዘብ የማከፋፈል ሥራን በመወጣት በኩል ልምድ እንዳላቸው ተነግሯል።

ዴኒስ ፋይንበርግ ከዚህ ቀደም ካከናወኗቸው ተመሳሳይ ተግባራት መካከል ለአሜሪካ የመስከረም አንዱ የሽብር ጥቃት ሰለባዎችና ዲፕዋተር ሆራይዘን ለተሰኘ የነዳጅ ዘይት ፍሳሽ የቀረቡ የገንዘብ ድጋፎችን በአግባቡ ፈጽመዋል ተብሏል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)