አሜሪካ ወደ ሀገሯ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር በግማሽ ልትቀንስ ነው

የአሜሪካ መንግሥት ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ የስደተኞችን ቁጥር በግማሽ እንደሚቀንስ አስታወቀ።

በቀጣዮቹ 12 ወራት 18 ሺህ ስደተኞችን ብቻ በሀገሪቱ የስደተኞች መርሀግብር መሰረት እንደሚቀበል የተናገረ ሲሆን፣ ይህም በታሪክ ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ ሁኔታ ትንሹ ተብሏል።

የአሜሪካ ጦርን ለረዱ ኢራቃውያን የተወሰነ ቦታ መያዙ የተገለፀ ሲሆን፣ በሀገራቸው በእምነታቸው ምክንያት ለተገፉና ለተሰደዱ ሰዎችም የተወሰነ ኮታ መያዙ ተሰምቷል።

ይህንን የአሜሪካ እርምጃ የሰብኣዊ መብት ተሟጋቾች ተችተውታል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግዛቶችና የአካባቢ አስተዳዳሪዎች በማህበረሰባቸው ውስጥ እነዚህን ስደተኞች ከሰፈራቸው እንዲያስወጧቸው የሚያስችላቸውን ትዕዛዝ ያረፈበት መመሪያ ፈርመዋል።

መመሪያው "ስደተኞቹ ሊረዷቸው፣ ሊደግፏቸውና በቀላሉ ከአሜሪካውያን ጋር እንዲቀራረቡ ከሚረዷቸው ማህበረሰብ አካባቢ ይሰፍራሉ" ይላል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ የስደተኞችን ቁጥር መቀነስ የአስተዳደራቸው ቀዳሚ ዓላማ መሆኑን ይናገራሉ።

እኤአ በ2017 አሜሪካ የምትቀበላቸውን የስደተኞች ቁጥር ወደ 50ሺህ ለመቀነስ የወሰኑ ሲሆን፣ በቀጣዩ ዓመት ደግሞ 40ሺህ፣ ከዚያም 30 ሺህ እንደሚሆን ወስነው ነበር።

በመግለጫቸው ላይም በደቡባዊ የሜክሲኮ ድንበር በኩል ወደ ሀገሪቱ እየገቡ ጥገኝነት የሚጠይቁ ሰዎች "ከአቅም በላይ የሆነ ጫና " መፍጠራቸውን ባለስልጣናት መናገራቸውን ገልፀዋል።

"በአሁኑ ሰዓት ያለው የአሜሪካ የስደተኞች ስርዓት ጫና ሌላ ነው፤ በርካታ ስደተኛ ከመቀበላችን በፊት መሻሻል አለበት" ብሏል ይህን ጉዳይ በኃላፊነት የሚመራው ቢሮ በመግለጫው።

አሜሪካውያንን ለረዱ ኢራቃውን 5ሺህ፣ ከጓቲማላ፣ ሆንዱራስ፣ ኤል ሳልቫዶር በሐይማኖታቸው ምክንያት መድረሻ አጥተው ለተሰደዱ 1ሺህ 500 ቦታ ተይዞላቸዋል።

የሰብዓዊ ርዳታ አቅራቢዎች ይህንን ርምጃ ለመተቸት የቀደማቸው አልነበረም።

"ይህ ለአሜሪካ ጥቁር ቀን ነው" ያሉት የዓለም አቀፉ ሬስኪዩ ኮሚቴ የበላይ ኃላፊ ዴቪድ ሚሊባንድ ናቸው።

ሌሎች የዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም አሜሪካ በዓለም ላይ ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ለመከላከልና ከለላ ለመስጠት ፍላጎት አለማሳየቷ የወደፊት ጥቅሟን ይጎዳዋል ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡