በግሪክ ሞሪያ የስደተኞች ካምፕ በተነሳው እሳት የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉ ተገለጸ

በግሪኳ ደሴት ሌስቦስ በከፍተኛ ሁኔታ በተጨናነቀው የሞሪያ ስደተኞች ካምፕ በተነሳው እሳት ቢያንስ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን የአገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ባለሥልጣናቱ እንዳሉት የሟቿ ሴት አስክሬን በሞሪያ ካምፕ ውስጥ የተገኘ ሲሆን፣ ማረጋገጥ ባይቻልም ሌላ አንድ ሕፃንም ሳይሞት እንዳልቀረ ተነግሯል።

አደጋው ሲከሰት የእሳት አደጋ ሠራተኞች በጣም ዘግይተው ነው የደረሱት በማለት ተቃውሟቸውን ባሰሙት ስደተኞች ላይ ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ ተኩሷል።

የስደተኞች ካምፑ መያዝ የሚችለው 3 ሺህ የሚሆኑ ስደተኞችን ቢሆንም፤ 12 ሺህ የሚሆኑ ስደተኞች በድንኳንና በእቃ ማጓጓዣ ኮንቴይነር ውስጥ ይኖሩበታል። ይህም መጨናነቅንና መተፋፈግን ፈጥሯል።

ባሳለፍነው ዓመት የቢቢሲዋ ቪክቶሪያ ደርብይሻየር ፕሮግራም በካምፑ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ካጋለጠ በኋላ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ ግሪክ ጥገኝነት ፈላጊ ስደተኞችን ከሌስቦስ እንዲያስወጣ አሳስቦ እንደነበር ይታወሳል።

የግሪኳ ደሴት ሌስቦስ የስደተኞች ቀውስ የምታስተናግድ ከተማ ናት። ግሪክ ባለፉት ሳምንታት በቱርክ አድርገው ወደ አገሪቷ የሚገቡ ስደተኞች መልሶ ለማቋቋም እየሰራች ትገኛለች።

በጎርጎሳውያኑ 2015 በሶሪያ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች በጎረቤት አገር ቱርክ አድርገው ወደ ግሪኳ ደሴት መግባታቸው ተገልጿል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)