የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በስድስት ወር ከ90 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገልጿል፡፡
ባለስልጣኑ የ2010 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን ለተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል።
በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ከአገር ውስጥ ታክሶች፣ ከውጭ ንግድ ቀረጥና ታክሶች፣ ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች እንዲሁም ከሎተሪ ሽያጭ የተጣራ ትርፍ በአጠቃላይ 109 ነጥብ 36 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ወደ ስራ መግባቱን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሞገስ ባልቻ ገልጸዋል፡፡
ይሁንና በግማሽ ዓመቱ ለመሰብሰብ ከታቀደው ውስጥ 90 ነጥብ 81 ቢሊዮን ብር የታክስ ገቢ የሰበሰበ ሲሆን ይህም የእቅዱን 83 ነጥብ 04 በመቶ አሳክቷል።
የተሰበሰበው ገቢ ከአገር ውስጥ ታክስ የ56 ነጥብ 45፣ ከውጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ ገቢ የ43 ነጥብ 46፣ እና ከሎተሪ ሽያጭ የተጣራ ገቢ የ0 ነጥብ 10 በመቶ ድርሻ አላቸው።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ አፈጻጸሙ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ 12 ነጥብ 02 በመቶ ዕድገት አሳይቷል።
ለዕቅዱ ሙሉ ለሙሉ አለመሳካት ተቋሙ ማከናወን ያለበትን ዝርዝር የገቢ ስራዎች በተሟላ ሁኔታ አለመፈጸም በተለይ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት በዝግጅት ምዕራፍ ጊዜ መውሰዳቸው በምክንያትነት ተጠቅሷል። ዘገባዉ የኢዜአ ነው፡፡