ኢ ነመራ
አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ በቅዳሜ ሕዳር 09/2004 ዕትሙ |እውነት ይህ አገር የማን ነው? ክፍል 2´ በሚል ርዕስ በማኔጂንግ ኤዲተሩ ዳዊት ከበደ የቀረበ ፅሁፍ አስነብቦናል፡፡ቀዳሚው ክፍል 1 ከሁለት ወር ያህል ቀደም ብሎ መስከረም13፣2004 ዓ/ም ነበር የተፃፈው፡፡
የፅሁፉ ክፍል 1 ያተኮረው በመስከረም ወር ላይ በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦችና ይህ ሁኔታ ፈጠረው የተባለው ድባብ ላይ ነው፡፡ ፀሐፊው ዳዊት በጉዳዩ ላይ የፌዴራል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማልና የፌዴራል ፖሊስ ም/ኮምሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤል የሰጡትን መግለጫ እንደመነሻ ተጠቅሟል።
አቶ ሽመልስ “ከፀረ ሰላም ሀይሎች ጋር በመሆን በአገራችን የሽብር መረብ በመዘርጋት የሰላማዊ ዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ ለመጣል አሲረዋል” በሚል የተጠረጠሩ ሰዎች መኖራቸውን መግለፃቸውን አንስቶ፣ “በዚህች አገር ምን እየተፈጠረ እንደሆነ አልገባህ አለኝ” ብሎናል፡፡ አቶ ሽመልስና ኮማንደር ደመላሽ የሚሉት ሽብር የት ጋ እንደሆነ ለማየት እና/ ወይም ለማዳመጥ በሌሊት የቤቱን መስኮት ከፍቶ ቢያዳምጥ፣ እንኳን ጦርነትና ሽብር ምንም አልሰማ እንዳለው፣ ከተማዋ ፀጥ ረጭ ማለቷንም ነግሮናል።
ዳዊት የመንግስት ባለስልጣናቱ “መኖሩን ደርሰንበታል” ያሉትን እጅግ ረቂቅ በሆነ ሚስጢራዊ መንገድ፣ ዘመናዊ የመገናኛ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚከናወነውን በአሸባሪዎች የሚፈፀም የአሸባሪዎች ድርጊት፣ ከቤቱ ሆኖ በመስኮት አለማየቱ እንዳሰገረመው እየነገረን መሆኑን ልብ በሉ። ይህን እንደሳር ውስጥ እባብ ሳር መስሎ ሳናየው፣ እየተሽሎከለከ ሳንሰማው እንደ እባብ እየተጠጋን የነበረውን ሽብር ግን፣ ድምፃቸውን ውጠው የሚጠብቁት ነበሩ። የሁለቱን ፍልሚያ እንኳን ቤታችን ሆነን በመስኮት ልናየው ቀርቶ፣ መሃከልም ሆነን ልናስተውለው አንችልም። ሽብርተኝነትን አስፈሪ የሚያደርገው ይህ ባህሪው አይደል? በቅርቡ አቃቤ ህግ ለፍ/ቤት ያቀረበው በዚህ ፀጥታ መሃከል የተያዘ የአደጋ መልዕክት ልውውጥ ድምፅ ግን ስውር የነበረውን አደጋ አሰምቶናል፡፡ጋዜጠኛ ዳዊት ይሄን የቤቱ መስኮት ላይ ሆኖ አልሰማ ያለውን የሽብር ሁካታ ሲሰማ ይሆን “ይህን ከምሰማ አገር ጥዬ ብጠፋ ይሻላል” ብሎ የኮበለለው?
ያም ሆነ ይህ የዚህ ፅሁፍ ትኩረት ዳዊት ከወራት በፊት ያቀረበው “እውነት ይህ አገር የማንነው?” የሚል ፅሁፍ ሳይሆን፣ ክፍል 2 በሚል በተመሳሳይ ርዕስ ያቀረበልን በመሆኑ እዚሁ ላይ ላተኩር።
ክፍል 2 “እውነት ይህ አገር የማነው?” በሚል የቀረበው የጋዜጠኛ ዳዊት ፅሁፍ አገር ጥሎ ለመፈርጠጥ ያኮበከበበት መሆኑን፤ ፅሁፉን ባነበብን በሁለተኛው ቀን ላይ ነው ያወቅነው። ዳዊት “አገሬን ቀማችሁኝ” እያለን ነው፡፡ እንደእኔ አተያይ ደግሞ አገራችንን ለመንጠቅ የተሰጠውን ተልዕኮ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለማስፈፀም ተፍጨርጭሮ እንደማያዋጣ ሲያውቅ፣ አሊያም ስራውን ስለሚያውቀው የህግ በትር አስደንብሮት ለስደት የበቃ ይመስለኛል። ይህን መጨረሻ ላይ እመለስበታለሁ። አሁን “የአገሬን ባለቤትነት ተነጠኩ” የሚለውን መላምቱን ያስረዳልኛል በሚል ያቀረበውን ክፍል 2 “ዕውነት ይህ አገር የማነው?” ወደሚለው ፅሁፍ እንመለስ፡፡
በቅድሚያ ግን እርሱ በፅሁፉ ላይ መልስ ሳይሰጥበት በርዕሱ ላይ ላነሳው |እውነት ይህ አገር የማነው?´ የሚለው ጥያቄ ላይ የተጠቀሰውን የአገር ምንነት በአጭሩ ለመመልከት እሞክራለሁ።
አገር፤ ግኡዙ መሬት፣ ሜዳው፣ ጋራው፣ ሸለቆው ወንዙ፣ ኃይቁ … አይደለም፡፡ ሰው አልባ መሬት አገር አይደለም፣ አይሆንምም፡፡ መሬትን አገር የሚያሰኘው በላዩ ላይ የሚኖረው ሰው ነው፡፡ይህም አገር በግኡዝ መሬት ላይ ወሰን ከልሎ የሚኖረው ሕዝብ መሆኑን ያመለክታል። ስለአገር ነፃነት፣ ስለሰበአዊ መብት፣ ብልፅግና … ስናወራም፣ በመሬት ላይ በዚህ መልክዓምድራዊ ወሰን ውስጥ ስለሚኖሩት፣ ሰዎች ግለሰባዊና ማህበራዊ ማንነት፣ መብቶች ነፃነቶችና ፍላጎቶች ነው የምናወራው።
አገር ግኡዝ መሬት፤ ሜዳ፣ ተራራ፣ ወንዝ……ብቻ እንደሆነ ተደርጎ የሚቆጠረው ለተስፋፊና ወራሪ አምባገነናዊ የመንግስት ስርአት ብቻ ነው፡፡ቀደም ሲል በኢትዮጵያ የነበሩት ዘውዳዊና ወታደራዊ አምባገነን የመንግስት ስርአቶች ስለ አገር የነበራቸው አይነት ግንዛቤ መሆኑ ነው፡፡ሁለቱ አምባገነን የመንግስት ስርአቶች ስለአገር አንድነትና ነፃነት ሲያወሩ፣ መሬቱ በላዩ ላይ ሰው የሌለው ይመስል፣ ሰዉን ትተው በምድር ላይ ስለተከለለው የወሰን አንድነትና ይህ ወሰን በእነርሱ ቁጥጥር ስር መሆኑ ላይ ነበር የሚያተኩሩት፡፡ እንደዛማ ባይሆን፣ ከ20 በላይ በብሄራዊ ማንነት ተደራጅተው የትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ ዜጎች እሪታ ይሰማቸው ነበር፡፡
ለመንደርደሪያ ያህል ስለአገር ይህን ያህል ካነሳሁ ጋዜጠኛ ዳዊት ጠይቆ ሳይመልስ ወደተወው የባለአገሩ ማንነት ልመልስ።በፅሁፉ ላይ |ይህ አገር …´ብሎ ሲጠቅስ ኢትዮጵያን እየጠቀሰ ስለሆነ “ኢትዮጵያ እንደ አገር ማን ነች? የማንስ ነች?’’ የሚለውን ነው የማነሳው፡፡
ኢትዮጵያ የየራሳቸው ብሔራዊ ማንነት፤ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ ኖሯቸው በየራሳቸው መልክአምድራዊ ወሰን ላይ የሚኖሩ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ የሚኖሩባት ግዙፍ ፖለቲካዊ ማህበረሰብ ናት። ይህ ግዙፍ ፖለቲካዊ ማህበረሰብ የራሱ የሆነ መልክአምድራዊ ወሰን አለው፡፡
የዚህች ኢትዮጵያ ባለቤቶች፣ እነዚህ የተለያየ መገለጫዎች ያላቸው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አባላት የሆኑ ግለሰባዊና የቡድን ማንነት፣ መብቶችና ነፃነቶች ኖሯቸው በአንድ የመንግስት ስርአት ስር የሚኖሩ ዜጎች ናቸው። እነዚህ የሚኖሩበትን መሬት አገር ያሰኙ ኢትዮጵያውያን ዜጎች በእኩልነትና በመከባበር በአንድ መንግስት ስር እየተዳደሩ ለመኖር ቃል ገብተው የቃል ኪዳን ሰነድ ቀርፀዋል፤ የኢፌዴሪ ሕገመንግትን።
የዚህች አገር ባለቤቶች፣ ህገመንግስቱን የቀረጹና በሀገመንግስቱ መሰረት የመኖር፣ የማክበርና የማስከበር ቃልኪዳን ያላቸው ሁሉም ዜጎች ናቸው፡፡እነዚህ ኢትዮጵያውያን ብቸኛ የመንግት ስልጣን ምንጭና ባለበቶችም ናቸው።ይህን ስልጣን በሕገመንግስቱ መሰረት ፣ ሊያስተዳድረን ይችላል ላሉት ወገን በውክልና ይሰጣሉ፡፡ በውክልና ስልጣን የሚረከበውም መንግስት በሕገመንግስቱ መሰረት የመፈጸምና የማስፈፀም ኃላፊነትና ግዴታ አለበት። ሕገመንግስቱን ማስፈፀም ያስችለኛል የሚላቸውን ህጎችና ፖሊሲዎች ከህገመንግስቱ ጋር ሳይጣረሱ የማውጣትና የማስፈፀምም ስልጣን አለው።ኢትዮጵያና የመንግስት ስርአቷ ይህን ይመስላል፡፡
የማንኛውም ግለሰብ፣ ወይም ቡድን ፍላጎትና አመለካከት ዋነኛ የህዝብ የበላይነት መገለጫ ከሆነው ህገመንግስትና ህገመንግስታዊ ስርዓት የበላይ ሊሆን አይችልም፡፡ ማንኛውም ቡድን ወይም ግለሰብ ህገመንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ህገመንግስታዊ ባልሆነ መንግድ የማፍረስ መብትና ነፃነት የለውም። ይህን የህዝብ የበላይነት መገለጫ የሆነ ህገመንግስትና ህገመንግስታዊ ስርዓት ማስከበር ደግሞ በስልጣን ላይ ያለ መንግስት ሃላፊነትና ግዴታ ነው።
ማንኛውም የህገመንግስታዊ ስርዓቱ አባል የሆነ ዜጋ ግን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አግባብ የፈቀደውን አመለካከት የመያዝ በአመለካከቱ የመደራጀት፣ በግልና በጋራ አመለካከቱን የመግለፅ፣ በሰላማዊ መንገድ የህገመንግስቱን ድንጋጌዎችም የመተቸት፣ ህዝብ እንዲያሻሽላቸው የመጠየቅ፣ በአቋምና በአመለካከቱ ለፖለቲካ ስልጣን የመወዳደር፣ በአብላጫ የህዝብ ድምፅ በሚገኝ ውክልና ብቻ የመንግስት ስልጣን የመረከብ መብት አለው፡፡ እነዚህ መብቶች ህገመንግስታዊ መብቶች ናቸው።
ጋዜጠኛ ዳዊት፣ ምላሽ ሳይሰጥበት የፅሁፉ ርዕስ መግቢያ ያደረገው የኢትዮጵያ ባለቤት ማነው? የሚለው ጥያቄ ከላይ ከተገለፀው መርህ አኳያ የሚታይ ነው። ዳዊት “እውነት ይህ አገር የማነው?’’ የሚለውን ጥያቄውን ያነሳው ከልቡ ምላሹን አጥቶት ነው የሚል ግምት የለኝም፡፡ ከዚህ ይልቅ “እኔና ጓደኞቼ የባለአገርነት መብት ተነፍገን” የሚለውን የግል ስሜቱን ሊገልፅልን ፈልጎ መሆኑን አገነዘባለሁ።
መሰደዱን ከማሳወቁ ከቀናት በፊት ባስነበበን ፅሁፍ የአገር ባለቤትነት መነፈጉን፣ በዚህም ማዘኑን ነግሮን እኛም እንድናዝን እንድናስተዛዝነውም |ነፃነትን ለመሸመት ስደት፣ የጋዜጠኝነት ሙያ ህገመንግስታዊ መብት ወይስ ውንጀላ፣ እስክንድር በቃሊቲ እና ሁለት አመት የዘገየው ድግስ´ በሚሉ ንኡስ ርዕሶች ሙሾውን አውርዷል።
|ነፃነትን ለመሸመት ስደት´ ´በሚለው ንኡስ ርዕስ ስር፣ በቅርቡ “መንግስት አስፈራራኝ’’ ብሎ ከአገር መሰደዱ የተገለፀውን የሀፍትህ ጋዜጣ አምደኛ የአቤ ቶኪቻው (በብዕር ስም) አበበ ቶላን ጉዳይ በማንሳት ይጀምራል። መሰደዱ የተገለፀልን አቤ ቶኪቻው የተባለ ፀሐፊ አርብ ህዳር 1፣ 2004 ዓ/ም ወደእርሱ መጥቶ ያጋጠመውን እንዳጫወተው ዳዊት ገልፆልናል። አቤ ቶኪቻው “አጋጠመኝ’’ ብሎ የነገረውን ሲሰማ፣ መሰደዱ ይህ ካልሆነም መታሰሩ አይቀሬ መሆኑን መተንበዩን፣ ከቀናት በኋላ ትንቢቱ ይዞለት የአቤ ቶኪቻው ስደት ዕውን መሆኑን ነገረን፡፡
ዳዊት፣ አቤ ቶኪቻው “ገጠመኝ” ብሎ የነገረውን ለስደት ያበቃውን ምክንያት በፅሁፉ ላይ አልጠቀሰውም፡፡ ለአቤ ቶኪቻው ቅርብ የሆነው ፍትህ ጋዜጣ በህዳር 8 ዕትሙ ስለነገረን ይህንኑ ጠቅሰን እንመልከት። አቤ ቶኪቻው ለስደቱ ምክንያት ብሎ ለፍትህ ጋዜጣ የገለፀው፣ የደህንነት ባልደረባ መሆኑን መታወቂያውን አሳይቶ ማንነቱን እንዳሳወቀው የገለፀው አንድ ግለሰብ በጋዜጣ ላይ የሚፅፈውን ፅሁፍ እንዲያቆም ሙከራ ማድረጉን ነግሮናል። ይሄው |የደህንነት ባልደረባ´ መሆኑን አሳውቆኛል ያለው ግለሰብ፣ ከመሰደዱ በፊት በነበረው ሳምንት አጋማሽ ላይ “ለረጅም ጊዜ ከእኛ ጋር አብረህ ትሰራለህ ብለን አስበን ነበር። አንተ ግን የምትመለስ አይደለህም። እናም ከእንግዲህ በኋላ አለቆቼ ሊከሱህ እየተዘጋጁ በመሆናቸው ውሣኔው ያንተው ነው” እንዳለውና አሁንም ይህን ሰምቶ ከሃገር መሰደዱንም ነግሮናል።
እንግዲህ ጋዜጠኛ ዳዊት ከነጓደኞቹ “የአገር ባለቤትነት መብታችን ተነፈግን” ብሎ መበደሉን ለማረጋገጥ የጠቀሰው አቤ ቶኪቻው ከአገር የተሰደደው በዚህ አኳኋን ነው። ልብ በሉ አንድ ህግን ለማስከበር በሚስጥር መረጃን ለማሰባሰብ የተሰማራ የመረጃ ሰራተኛ፣ አቤ ቶኪቻውን የተከታተለው በሚስጥር እንዳልሆነ ነው የተነገረን፡፡ በጉልህ |የሚስጥር ዘበኛ´ የሚል ፅሁፍ መለዮው ላይ ፅፎ፣ የተሰወረ ህገወጥን የሚያነፈንፍ ነጭ ለባሽ ፖሊስ እንደማለት ነው። ይህ በፍፁም ሊሆን የማይችል፣ ሆኖም የማያውቅ ነው። የሚነገረው ውሸት መሆኑን እያወቀ ውሸቱን ለማመን ለፈቀደ ሰው ካልሆነ በስተቀር።
እርግጥ አቤ ቶኪቻውን የመረጃ ሰራተኛ ያልሆነ ሰው፣ “የመረጃ ሰራተኛ ነኝ” ብሎ እየተከታተለው መሆኑን ነግሮት ቢሆንስ፡፡ ይህን ያደረገበትም ዓላማ ሊኖረው እንደሚችል መገመትም ይቻላል፡፡ ፀሐፊ አቤ ቶኪቻው “መንግስት እየተከታተለኝ ነው” ብሎ በሌለ ነገር ደንብሮ ከአገር እንዲወጣ፣ ይህንንም “የመንግስት ግፍ” እንዲናገርና እንዲያስነግር የማድረግ አላማ። ሳይለፉ መንግስትን “ክፉ” የማስባል ዓላማውን የሚያሳካለት ሞኝ ካገኘ ምን ገዶት። የኢትዮጵያን ፖለቲካ በመተንተን ከኔ በላይ ላሳር የሚለው አቤ ቶኪቻው ይህን አምኖ መፍራቱ ግን ያስገርማል፤ አቤ ሞኝ ነበር ማለት ነው?
አቤ ቶኪቻው ለስደት አበቃኝ በሚል የነገረን ከላይ የሰፈረው ያቀረበው ሰበብ ከዚህ የተለየ ምክንያትም ሊኖረው ይችላል። ይህም እንደማንኛውም አሜሪካ ሄዶ መኖር የሚፈልግ የባእድ አገር ናፋቂ፣ “መንግስት አባረረኝ” የሚል ወሬ በሚዲያ አስወርቶ በጎረቤት አገር እረፍት አድርጎ በአውሮፓና በአሜሪካ የፖለቲካ ጥገኝነት ለማግኘት የሚያስችለውን የመግቢያ ቪዛ በእጁ የሚያስገባበት መላ ማመቻቸት።
ይህ የተለመደና የሚታወቅ የቪዛ ማግኛ አቋራጭ ስልት ነው። ወደጎረቤት አገር ተሰደው ከዚያ ወደ አሜሪካና ሌሎች የምዕራብ አውሮፓ አገራት ለመግባት የተለያየ ሰበብ አቅርበው ሳይሳካላቸው ቀርቶ እዛው ጎረቤት አገር ኑሯቸውን መስርተው ፣አዲስ ለሚመጡ ስደተኞች የማማከር አገልግሎት የሚሰጡና |ኬዝ´ እየፈጠሩ በመሸጥ የሚተዳደሩ ኢትዮጵያውያን ለ|ደንበኞቻቸው´ የሚመክሩዋቸው ቀላሉ የቪዛ ማግኛ መንገድ ይሄው “መንግስት አባረረኝ መግቢያ አሳጣኝ፣ ፈለጠኝ ቆረጠኝ …” የሚለውን ነገር በመገናኛ ብዙሀን እንዲያስወሩ ማድረግ መሆኑ ይታወቃል። እናም አቤ ቶኪቻው |መንግስት አባረረኝ´ ለማለት ያቀረበውን ምክንያት ከላይ ከተገለፀው ዕውነታ አኳያ ስናየው ስደቱ ነፃነትን የመሸመት ስደት ሳይሆን፣ አንድም የሞኝነት፣ አንድም የቪዛ ፍለጋ ስደት አይሆን ይሆን? ወይም “በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚሰራ ጋዜጠኛ” ተብሎ ለመሸለም።
ዳዊት አዲስአበባ ውስጥ ተቀምጦ፣ ህግንም፣ የሞያ ስነምግባርንም ከቁብ ሳይቆጥር ያሻውን እየቀባጠረ፣ ልክ ኤርትራ ውስጥ ይሰራ የነበረ ጋዜጠኛ ይመስል “በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚሰራ ጋዜጠኛ” በሚል በሲፒጄ እንደተሸለመው ማለት ነው፡፡ በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ይሰራል የተባለው ዳዊት የኢትዮጵያን መንግስት ፓስፖርት ይዞ፣ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል በኢትዮጰያ አየር መንግድ አውሮፕላን ተሳፍሮ ወደ አሜሪካ በርሮ፤ ይህን ሁሉ ውጣ ውረድ አልፎ ሽልማቱን ተቀብሎ ተመልሷል፡፡ እንዲህም አድርጎ ፈተና የለም፡፡
ዳዊት ሁለተኛው የአገር ባለቤትነት መብቱን ማጣቱን ያሳይልኛል በሚል የቀረበው |የጋዜጠኝነት ሙያ ሕገመንግስታዊ መብት ወይስ ወንጀል?´ በሚል ንኡስ ርዕስ ሥር የቀረበው ፅሁፍ ነው፡፡ ይህ ፅሁፍ በዛሬዋ ኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ፤ በአንድ በኩል ሕገመንግስታዊ መብት በሌላ በኩል ደግሞ ወንጀል መሆኑ በግልፅ እየተነገረን ነው። መብት አሊያም ወንጀል መሆኑ የሚወሰነው ኢህአዴግ ለግለሰቡ (ለጋዜጠኛው) ባለው አዎንታዊ አሊያም አሉታዊ አመለካከት ብቻ ነው ´ ብሎ ይጀምራል።
ይህንንም ሲያብራራ ከሁለት ወር በፊት ክፍል 1 “እውነት ይህ አገር የማን ነው?” በሚል ርዕስ ፅሁፍ ባቀረበበት ወቅት እከሌ የታሰረው ከጋዜጠኝነት ሙያው ውጭ በሽብር ድርጊት በመሳተፉ ነው የሚል ዜና ይስተጋባ እንደነበር አስታውሶ፣ አንድ የዋህ ጋዜጠኛ በዚህ አባባል በጋዜጠኝነቴ በሰነዘርኩት ትችት አልታሰርም ህገ መንግስታዊ ከለላ አለኝ በሚል ዕምነት |መንግስትን የማያስደስት´ መጣጥፍ ካሰፈረ |የጋዜጠኝነትን ሙያና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን እንደሽፋን በመጠቀም … ´ በሚል “በሚዲያ ይተቻል” ብሏል።
ዳዊት የገለፀውን ከላይ የተጠቀሰ ሃሳብ ሁለት ገፅታዎች አሉት። የመጀመሪያው ሐሳብን የመግለፅ ሕገመንግስታዊ መብትንና ወንጀልን የሚመለከት ነው፡፡ ሌላኛው አንድ በሚዲያ የተገለፀ ሃሳብ ላይ በሚዲያ የሚቀርብ የመልስ ትችትን የሚመለከት ነው።
በህገ መንግስቱ መሰረት ማንኛውም ጋዜጠኛ እንደ ዜጋ ካለምንም ቅደመ ምርመራ ያመነበትን ሃሳብ በሚዲያ የማስተላለፍ፣ መረጃ የማግኘት መብት አለው። ይህ መብት በተለይ ለጋዜጠኛ ብቻ የተሰጠ ሳይሆን የማንኛውም ዜጋ መብት ነው። ጋዜጠኛን ልዩ የሚያደርገው መረጃን ሰብስቦ ማስተላለፍ ዋና ሞያው መሆኑ፣ እግረ መንገዱንም አቋሙን የመግለፅ እድል ያለው መሆኑ ብቻ ነው። ጋዜጠኛ በመሆኑ ከሌላ ዜጋ የተለየ ሕገመንግስታዊ መብት የለውም።
ከጋዜጠኝነቱ ውጭ እንደማንኛውም ሰው – አባት፤ ባል ወንድም፣ ጎረቤት… ሆኖ ሲኖር፣ በህግ የተከለከለን ድርጊት ፈፅሞ ሲገኝ በወንጀል ይጠየቃል፡፡ ጋዜጠኛ በመሆኑ ህግ የመተላለፍ ልዩ መብት የለውም፡፡ እንደጋዜጠኛ፣ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነትን አጠቃቀም በተመለከተ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 22 ንዑስ አንቀፅ 7 እንዲሁም ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የወጡ ህጎችን ተላልፎ ሲገኝ በህግ ይጠየቃል፡፡ ተገቢ ያልሆነ መረጃና ሃሳብ ሲያስተላልፍ፣ በመገናኛ ብዙሀን ሊተች ሊወቀስ ይችላል።
እናም ጋዜጠኛ ዳዊት አንደኛ፣ ጋዜጠኞች ሀሳብን በነፃነት የመግለፅና፣ መረጃን የማስተላለፍ ህገ መንግስታዊ መብታቸው፣ የሌሎችን ዜጎች ህገ መንግስታዊ ፖለቲካዊና ሰብአዊ መብቶች ለማስከበርና ለመጠበቅ የወጡ ህጎችን የመጣስ መብት አላቸው የሚለውን እንደማያመለክት ማስታወስ ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ ሞያቸው ጋዜጠኝነት የሆኑ ሰዎች፣ በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ሲውሉ፣ የታሰሩት በሚሰሩበት ጋዜጣ ላይ ባስተላለፉት ሃሳብ አይደለም መባሉ ትክክል ነው፤ ማስረጃው ይህን እስካመለከተ ድረስ።
ጋዜጠኞች በሽብርተኝነት፣ ወይም በሌላ ማንኛውም ወንጀል – በስርቆት፣ በነፍስ ግድያ፣ በአስገድዶ መድፈር … ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ሲውሉ “በቁጥጥር ስር ለመዋል ያበቃቸው በጋዜጠኝነታቸው በሰሩት ስራ አይደለም” ተብሎ መገለፁ፣ እንደጋዜጠኛ በሚያስተላልፉት ሃሳብ ወንጀልንና ወንጀለኛን ቢያበረታቱ፣ ለወንጀለኞች ሽፋን ቢሰጡም በህግ አይጠየቁም፤ አይተቹም ማለት አይደለም፡፡
ዳዊት ባቀረበው ፅሁፍ “ለምን በመገናኛ ብዙሀን ተተቸሁ” የሚል ምሬት ያቀረበም ይመስላል። እርሱ ያለውን ትክክል ያልመሰለውን ነገር የመተቸት መብት፣ ሌላው ማንኛውም ዜጋ ያለው መሆኑን ለምን ዘነጋ? በህዝብ ድምፅ በተገኘ የስልጣን ውክልና የተሰየመውን ይህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፣ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጭምር እስከመዝለፍ በዘለቀ አኳኋን ሲተች፣ ሌሎች ዜጎች እርሱን የመተቸት መብት ያላቸው መሆኑንስ ለምን ዘነጋ? ይህ ሁኔታ ከአመታት በፊት በይፋ ባስተላለፈው |የእኔንና መሰሎቼን ሃሳብ የያዙ ጋዜጦችን፣ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ካልሆነ አታንብቡ፣ አታዳምጡ፣ አትመልከቱ ´በሚል ለፍፎት የነበረው ፀረ ሃሳብን የመግለፅ አቋም አሁንም ያልተለወጠ መሆኑን ያመለክታል፡፡
ዳዊት ፅሁፉን ቀጥሎ፣ |እስክንድር በቃሊቲ´ በሚል ንኡስ ስር እስክንድር ነጋን ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሔዶ እንደጠየቀው ነግሮን፣ ገድለ እስክንድር ነጋን አስነብቦናል፡፡ እስክንድር ነጋን ታዋቂው ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተንታኝ ሲል አሞካሽቶታል። እርግጥ ዳዊት ያሻውን ሰው የማሞካሸት መብት እንዳለው እቀበላለሁ፡፡ ሀኖም የእስክንድር ድንቅ የፖለቲካ ተንታኝነት በቅርቡ “በ2004 ዓ/ም መንግስትን ለመገልበጥ ተነሱ” በሚል ባስተላለፈው ጥናት ተብዬ 9 ገፅ ጽሁፍ ላይ ባቀረበው ውዳሴ ንጉሳዊ የመንግስት ስርዓት በርካታ ኢትዮጵያውያን በእጅጉ የታዘብነው መሆኑን ላስታውሰው እወዳለሁ፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ዘውዳዊው ስርአት፣ የኢትዮጵያን ህዝብ የአገር ባለቤትነት መብቱን ቀምቶት እንደነበረ በሃዘን እናስታውሳለን። እስክንድር የኢትዮጵያ ህዝብ ዘውዳዊውን ስርዓት ከስሩ ነቅሎ ዳግም በማያንሰራራበት ሁኔታ ቀብሮት ከበሰበሰ ከአንድ ትውልድ ዕድሜ በኋላ ለትንሳዔው ያስተላለፈውን ጥሪ ስንሰማ “አሁን ላይ የሞተን ዘመን የሚኖር ያፈጀ ወጣት” ብለነዋል ።
ዳዊት ዝክረ እስክንድር ነጋን ባቀረበበት የፅሁፍ ክፍል ፣ “እስክንድር ይህ አይነቱ እስርና መጎሳቆል ሊመጣ እንደሚችል አስቀድሞ ያውቀው ነበር” ብሎናል። ይህ ልክ ሊሆን ይችላል፤ አንድን ድርጊት ከባለቤቱ በላይ የሚያውቅ ስለሌለ፣ ስራው የሚያስከትለውን ውጤት ስለሚያውቅ ይሆናል መታሰሩን ያወቀው። ዳዊት ሊለን የፈለገው “አስቀድሞ ሊያሳስረው አንደሚችል ያወቀው ስራው ወንጀል አይደለም” የሚለውን ከሆነ፣ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ስለተያዘ የፍርድ ሂደት ላይ ከሳሽ አቃቤ ህግ የሚያቀርበውን የጥፋተኝነት ማስረጃ፣ እንዲሁም ተከሳሽ እስክንድር የሚያቀርበውን መከላከያ ካዳመጥን በኋላ ብንናገር ተገቢ ይመስለኛል።
ዳዊት በጽሁፉ ማሳረጊያ ላይ “ሁለት አመት የዘገየው ድግስ” በሚል ርዕስ በቅርቡ በሌሉበት የተከሰሱትን የቀድሞ የአዲስ ነገር ጋዜጣ አዘጋጆች አቢይ ተክለማርያምና መስፍን ነጋሽን ጉዳይ አንስቷል። አቃቤ ህገ በሁለቱ ግለሰቦቸ ላይ ያቀረበውን ክስ፣ ከሁለት አመት በፊት “መንግስት እየተከታተለን ነው” ብለው ጮኸው፤ አስጩኸው ከአገር በተሰደዱ ጊዜ “የተደገሰላቸው ምን እንደነበር የሚያሳብቅ ነው” ብላል።
አብይ ተክለማርያም መከሰሱን ሲሰማ |በማለዳ ተነስቼ ሰለአገሬ ባሰላሰልኩና በተወያየሁ፣ አገሬ ቃል ኪዳኖቿን እንድታሳካና እምቅ አቅሟን እንድትጠቀም ባለምኩኝ በአቶ መለስ ዜናዊ የሽብርተኝነት ክስ ተደገሰልኝ´ አለ ብሎናል፣ ዳዊት በፅሁፉ።
መቼም አብይ የቀረበበትን ክስ “ትክክልና ተገቢ ነው” ብሎ እንደማይቀበል ይታወቃል፡፡በመሆኑም “አለ” ተብሎ የተነገረን የሚደንቅ አይደለም፡፡ ዳዊት ክሱ ከሁለት ዓመት በፊት የተደገሰላቸው ምን እንደነበረ ያሳብቃል ብሎ ንፁህነቱን ብቻ ሊያስረዳን ከመሞከር ይልቅ፣ አቃቤ ህግ በምንና መቼ በፈፀሙት ወንጀል እንደከሰሳቸወም ነግሮን እንደጋዜጠኛ ሚዛናዊ መረጃ ቢያቀብለን መልካም ነበር።
ከዚህ ውጭ አብይ “ላገሬ ባሰብኩ ፤ እምቅ አቅሟን እንድትጠቀም ባለምኩ ምንትስ ምንትስ … ”በሚል የዘከዘከው ውሸት ነው፡፡ ቢያንስ አሁን በአገሪቱ ምንም በጎ ነገር እንዲሰራ እንደማይፈልግ ማስረጃ መጥቀስ ይቻላል።
አብይ ራሱ የሚያዘጋጀው “አዲስ ነገር” ይባል የነበረው ጋዜጣ ከሁለት አመት በፊት፣ ኢትዮጵያ በራስዋ አቅም ያስገነባችው፣ በወቅቱ ኃይል በማመንጨት አቅሙ በአገሪቱ ከፍተኛው የነበረውና በፕሮጀክቱ ግዙፍነትና ዘመናዊነት በዓለም ተጠቃሽ የሆነው የተከዜ የኃይል ማመንጫ ግድብ በተመረቀበት እለት ቅዳሜ ህዳር 5፣ 2002 ዓ/ም በወጣው እትሙ ላይ የቀረበን ፅሁፍ በአሰረጂነት እጠቅሳለሁ፡፡ በቅድሚያ በዚያን ዕለትና ሰሞን ከታተሙት ሁሉም የመንግስትና የግል የመገናኛ ብዙሃን፣ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃንን ጭምር፣ የግደቡን ግንባታ መጠናቀቅ ዜና ያልዘገበ ብቸኛ ጋዜጣ አዲስ ነገር ብቻ ነው።
አዲሰ ነገር ጋዜጣ በዚህ አላበቃም፡፡በዛው ግድቡ በተመረቀበት ዕለት ዕትሙ የግድቡን ግንባታ ጨምሮ ሌሎች ስኬቶቸን የሚዘግቡ ጋዜጠኞችን “ፎርፌ” በተሰኘው የቧልት አምዱ “ልማታዊ ጋዜጠኛ በገሃነም” በሚል ርዕስ ባቀረበው ፅሁፍ ፀያፍ ዘለፋ አቅርቧል፡፡ የኢትዮጵያን በጎ የማይፈቅዱ ቢጤዎቹን ፈገግ አሰኝቶ በስኬቱ ከተሰማቸው ሃዘን ሊያፅናና ያደረገው ሆኖ ይሰማኛል፡፡ “ለምን እንዲህ አደረክ” ብሎ የጠየቀው፣ የወቀሰውም አልነበረም፡፡ ህሊናውን ካልጎረበጠው መብቱ በመሆኑ፡፡ “አገር ወዳዱ” አብይ እንዲህም አድርጎ ኢትዮጵያ እምቅ አቅምን እንድትጠቀም ማለም የለም፡፡
አዲስ ነገር በወቅቱ “ልማታዊ ጋዜጠኛ በገሃነም” በሚል ርዕስ ባቀረበው ቧልት፤ “አንድ ልማታዊ ጋዜጠኛ ገሃነም ወርዶ“አገራችን እየተንቦገቦገች ነው፡፡ አገሪቱ ባለፉት ስድስት አመታት ያስመዘገበችው እድገት በጉልህ የሚታይ ነው፡፡ እሳቱ የሚፈጥረው ብርሃን ባለፈው አመት ተከስቶ የነበረውን የኤሌትሪክ ሃይል እጥረት እንዳቃለለው የኮርፖሬሽኑ ሃላፊ ነግረውናል፡፡ አሁን በግንባታ ላይ ያሉት ግድቦች ስራ ተጠናቆ ስራቸውን ሲጀምሩ አገሪቱ ለመንግሥተ ሰማያት የኤሌትሪክ ሃይል መሸጥ ትጀምራለች፡፡” ሲል ነበር የግድቡን ግንባታ ስኬት ያንጓጠጠው፡፡አብይ አሁን “አገሪቱ ዕምቅ አቅሟን እንድትጠቀም በተመኘሁ” ሲለን እየዋሸ መሆኑን የምንረዳው ለዚህ ነው፡፡
አሁን ዳዊት “አገሬን ተነጠኩ፣ መንግስት ሊያስረኝ መሆኑን ወፍ ነገረችኝ” ብሎ የጓደኞቹንም ገጠመኝ በአስረጂነት ጠቅሶ አገር ጥሎ የፈረጠጠው፣ እውነት አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በመስራት ላይ ከሚገኙ ጋዜጠኞች ሁሉ እርሱ ተነጥሎ የተበደለ ሆኖ አይደለም፡፡ ሩቅ ሆኖ እሳት መወርወሩ ይሻላል በሚል ግምት በራሱ ጊዜ ከሃገር መውጣት የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ለራሱ ነግሮ ሊሆን ይችላል፡፡እኛ ኢትዮጵያ ውስጥ የምንኖር ዜጎች ደግሞ፣ አንኳን ከሩቅ የሚወረወር ውስጣችን ከሚለኮስም እሳት ራሳችንን መጠበቅ አያቅተንም የሚል እመነት አለን፡፡
የኢትዮጵያን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጥቅምና ፍላጎት ያላገናዘበ እርሱ ግን እንዲኖር የሚፈልገው የመንግስት ስርአት አለመኖሩ፣ ሊኖር እንደማይችልም መገንዘቡ አገር እንደማጣት ተሰምቶት ሊሆንም ይችላል፡፡ለጓም አጥልቀውለት ሲጋልቡት የነበሩት፣ አልፎ አለፎም በሚያዘጋጀው ጋዜጣ ላይ ማንነታቸውን ሰውረው ያሻቸውን እንዲዘባርቁ ስሙንና ፎቶግራፉን ሲያውሳቸው የነበሩት ፈረንጅ አገር የሸፈቱ “ታጋዮች” መፈርጠጡን እንደ አንድ የትግል ስልት ሊጠቀሙበት አዘውትም ሊሆን ይችላል፡፡ የተለመደው ሂዩማን ራይትስ ዎች ያሰማን ጩኸት ይህን ያመለክታል፡፡ገና በዙ የቁራ ጩኸቶችንም እንጠብቃለን፡፡
ጋዜጠኛ ዳዊት ሣያስበው ባለማወቅ የገባበት አጣብቂኝ መሠደዱን የግድ አድርጎበት ሊሆንም ይችላል፡፡ ይህም ቢሆን አገሩን መነጠቁን አያመላክትም፡፡ እዚህ ላይ “ምን አይነት አጠብቂኝ ?” የሚል ጥያቄ መነሣቱ አይቀር ይሆናል፡፡ ዳዊት በማወቅም ይሁን ባለማወቅም አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሕገመንግስታዊ ሥርዓት አልወደደውም፡፡ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍቃዱ ተሰማምቶ የቀረፀውና የተቀበለው፣ እንዲጎለብትለትም የሚፈልግ ቢሆንም ለእርሱ ግን ቀልቡ አልደረሰም፡፡ ይህ መብቱ ነው፡፡ በሠላማዊ መንገድ ቅሬታውን መግለፅ፣ ከመሰሎቹ ጋር ተደራጅቶ ያመነበትን አቋም ማራመድ ይህን አቋሙን ይዞ ለሥልጣን የመፎካከርም መብት አለው፡፡ የማይችለው ይህን ሥርዓት ሕገመንግሥታዊ ባልሆኑ መንገድ ለመለወጥ መንቀሳቀስ ብቻ ነው፡፡
እዚህ ላይ ዳዊት ከላይ እንደተጠቀሰው ህገ መንግስታዊው ሥርዓት ስላልተመቸው ወይም የሚመቸው ስላልመሰለው ሊታገለው ወዷል፤ እንዲታገለው ተነግሮት ይህን ተቀብሏል፡፡ ስርአቱን በተመቸው መንግድ እንዲታገሉ ያሣመኑትና መታገያ መላ የሚያቀብሉት ወገኖች፣ “ጀግና” ሲሉ አወድሰውታል፣ እንዲሸለምም አድርገውታል፡፡ በዚህ ሁኔታ መሰላል አቀብለው ላይ የሰቀሉት አጋሮቹ፣ ሰቅለውት ሲያበቁ መሰላሉን ቀምተውታል፡፡ እንዳይወርድ መሠላሉ የለም፣ እንዳይቀጥል ያቀበሉት የትግል ሥልት ከሕግ ጋር ያላትመዋል፡፡ ከወጣበት “የታጋይነት” የዝና ማማ ላይ ዘሎ መውረዱ ክብርና ዝናውን መጣል ሆኖ ተሠምቶትም ሊሆን ይችላል፡፡ በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው ፍ/ቤት የቀረቡት ጓደኞቹ ላይ አቃቤ ሕግ የሚያቀርበውም ማስረጃ አስፈሪ ነው፡፡ “ያለምንም ማስረጃ ነው የታሠሩት ” እያለ ሲሸልል ለቆየው ዳዊት፡፡
በዚህ ሁኔታ ከወጣበት ማማ ማምለጫው መንገድ፣ ማማው ላይ ሲወጣ የተሰጠው የታጋይ ጋዜጠኝነት ክብሩ ሣይገፈፍ “አምልጬ መጣሁ” ብሎ ወደ ውጭ አገር መከኮብለል ነው፡፡ እናም “አገሬን ተቀምቼ መጣሁ” አላቸው፣ በታጋይ ጋዜጠኝነት ጀግና ብለው የሸለሙትም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ጋዜጣ ብቻ ያለ ይመስል፣ “….. ከሁለቱ አንዱ የሆነው የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር አገሩን ተነጥቆ ሌሎች አገራቸውን ተነጥቀው የተሰደዱ ጋዜጠኞችን ተቀላቀለ” ሲሉ አወጁለት፡፡ ሩቅ ሆነው ከአፍንጫቸው እልፍ በማይል ወንጭፍ ሕገመንግሥታዊውን ሥርዓት ለመናድ የሚንቀሳቀሱት፣ ያረጀና ያበቃለት የአመለካከት ማማ ላይ የተኮለኮሉ ጥቂት የጥፋት መልእክተኞችን ተቀላቀለ ማለት ነው፤ ይሄው ነው ታሪኩ፡፡