ኢትዮጵያ በሶማሊያ ላለው የአፍሪካ ኅብረት የሠላም አስከባሪ ኃይል ድጋፍ እንድታደርግ የኢጋድ መሪዎች ጠየቁ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2004/ዋኢማ/– ኢትዮጵያ በሶማሊያ ላለው የአፍሪካ ኅብረት የሠላም አስከባሪ ኃይል ድጋፍ እንድታደርግ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን /ኢጋድ/ አባል አገራት ጠየቁ፡፡

የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ኢንጂነር ማህቡብ ማዓሊም 19ኛው የኢጋድ መሪዎች ልዩ ጉባዔ ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ ከተካሄደ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ በሶማልያ ሠላምና መረጋጋት ለማስፈን ለተሰማራው የአፍሪካ ኅብረት የሠላም አስከባሪ ኃይል ድጋፍ እንድታደርግ መሪዎቹ መጠየቃቸውን ገልጸዋል፡፡

በምስራቅ አፍሪካ በተለይም የሶማልያ ሠላምና መረጋጋት እንዳይኖር የሚያተራምሰውን አሸባሪውን የአልሸባብ ቡድን የሽብር ድርጊት ለመግታት የኢትዮጵያ ድጋፍ ወሳኝ በመሆኑ ኢትዮጵያ ድጋፍ እንድታደርግ መሪዎቹ መጠየቃቸውን አመልክተዋል፡፡

የመሪዎቹ ጉባዔ የኬንያ የመከላከያ ኃይል ከሶማልያ የሽግግር መንግሥት ኃይሎች ጋር በመሆን በደቡባዊና ማዕከላዊ ሶማልያ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አድንቀዋል፡፡

ሁለቱ ኃይሎች የሚያካሂዱት ጥረት በአካባቢው ሠላምን ለማምጣት የተለየ አጋጣሚ እንደሚፈጥር መሪዎቹ መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡

በሶማልያ የተሰማራው የአፍሪካ ኅብረት ሠላም አስከባሪ ኃይላም ከነዚህ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት አሸባሪውን የአልሸባብ ቡድንን በማስወገድ በአገሪቱ ሰፍኖ የቆየው ሥርዓት አልበኝነት ፍጻሜ እንዲያገኝ የአከባቢው አገራት ትብብር ተጠናከሮ ሊቀጥል እንደሚገባው አስምረውበታል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኤርትራ መንግሥት እንደ አልሸባብ ላሉ አሸባሪዎች የሚያደርገውን ያልተቋረጠ ድጋፍ የኢጋድ መሪዎች ኮንነዋል፡፡

ኤርትራ የአካባቢውን አገራት ሠላምና መረጋጋት ለማናጋት ለሚንቀሳቀሱ አሸባሪዎች የምታደረገውን የጦር መሳሪያና ሌሎች ድጋፎችንም እንድታቆም ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል በቅርቡ ነፃ መንግሥት የመሰረተችውን የደቡብ ሱዳን ሪፓብሊክን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን /ኢጋድ/ አዲስ አባል አገር አድርጎ ተቀብሏታል፡፡

በሸራተን አዲስ የተካሄደው ልዩ የመሪዎች ጉባዔ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢጋድ ሊቀመንበር መለስ ዜናዊ የተመራ ሲሆን የኬንያው ፕሬዚዳንት ምዋይ ኪባኪ፣ የጂቡቲ ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌህና የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ፕሬዝዳንት ሼክ ሸሪፍ ሼክ አህመድ እንዲሁም የአባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተካፋይ ሆነዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡