ከቅርብ ግዜ ወዲህ በተለይ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን፣ ሰንበት ብሎ ደግሞ ወደባህርዳር ከተማና የጎጃም ዞን አንዳንድ ከተሞች እየተሸጋገረ የሄደ ሁከት እያስተዋልን ነው። እንግዲህ የዚህ ሁከት መነሻ የወልቃይት የአማራ ብሄረተኝነት ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ የአማራ ህዝብ ለዚህ ያለውን ተቃውሞ መግለጹ እንደሆነ ነው የሚነገረው። የዚህ ጉዳይ ዋነኛ ባለቤት እንደሆነ የሚናገረው የወልቃይት የአማራ ብሄረተኝነት ኮሚቴ ግን ድጋፉን ባይጠላውም አሁን እየተደረገ እንዳለው ንብረት አውዳሚ ሁከት እንዲቀሰቀስ ፍላጎት የለውም፤ ቢያንስ ፊት ለፊት የሚናገረው ይህንን ነው።
በተለይ የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ መክር ቤት የባለፉ 15 ዓመታት ጉዞውን እንዲሁም የሃገሪቱን ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ ገምግሞ ይፋ ባደረገው መግለጫ፣ የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ህገመንግስታዊ ምላሽ እንዲያገኝ እንደሚደረግ አስታውቋል። ማንም ከህገመንግስቱ ውጭ የመሆን ስልጣን ስለሌለውና ሃገሪቱን የሚገዛው ህገመንግስቱ ብቻ በመሆኑ ውሳኔው መሆን ያለበት ከህገመንግስቱ አንፃር መሆን ያለበት መሆኑ ተገቢ ነው።
ይሁን እንጂ ከዚህ ውሳኔም በኋላ ሁከት የመቀስቀስ ዝንባሌዎች መታየታቸው አላቆመም። mereja.com እና መሰል የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚጠቀምባቸው ማህበራዊ ሚዲያዎችም የብሄር ጥላቻ ቅስቀሳቸውንና የሁከት ዜናቸውን ማሰራጨታቸውን እንደተያያዙት ነው። የኤርትራ መንግስት የማህበራዊ ሚዲያዎች የሚያካሂዱት ቅስቀሳ ህገመንግስታዊ ስርአቱን የመናድ ሁከት እንዲቀሰቀስ ነው። የኤርትራ መንግስት የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚ የሆኑት እነ ግንቦት 7ም ሲመኙት የኖሩት የስርአት ለውጥ በሁከት እንዲመጣ የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ነው።
አንዳንድ በውጭ ሃገር የሚኖሩ ግለሰቦችም ከምክንያታዊነት ይልቅ በጭፍን ጥላቻ ላይ ተመስርተው ሁከት እያራገቡ ይገኛሉ። እነዚህ ከሃገራቸው ከወጡ ከአንድ ትውልድ እድሜ በላይ ያስቆጠሩ፣ ሃገሪቱንና ህዝቡን የማያውቁ ግለሰቦች ሃላፊነት በጎደለው ስሜት ስለሃገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ የመዘባረቅ ያህል የሚቆጠር ትንታኔ ሲሰጡ ይደመጣሉ። ይህ ነባራዊውን ሁኔታ ያላገናዘበ ወሬ ሃገር ውስጥ የሚገኙ በቀላሉ ውዥንብር ውስጥ ገብተው ረብሻ ለመቀስቀስ የሚመቻቹ የዋህ የሁከት አስፈፃሚዎች የልብ ልብ የሰጠበት ሁኔታ ይታያል። ይህ በውጭ ሃገራት በሚኖሩ አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች የሚካሄደውን የሁከትና ህገመንግስታዊ ስርአቱን የማፈረስ ቅስቀሳ ምን ያህል መሰረተ ቢስ እንደሆነ ለማሳየት ያህል በቅርቡ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ የተባሉ አንድ ግለሰብ በአሜሪካ ድምፅ የአማርኛ ፕሮግራም ከሰጡት አስተያየት መሃከል አንደ ሁለት ዋና ዋና ያለኳቸውን በዚህ ጽሁፍ ልመለከታቸው ወድጃለሁ።
ዶ/ር አረጋዊ ይሄ ስርአት ተወግዶ ህዝብን መሰረት ያደረገ፣ የህዝብን አመኔታ ያገኘ ህዝባዊ ፖለቲካዊ ስርአት ከሁሉም የፖለቲካ ሃይሎችና ሲቪክ ማህበራት የተውጣጣ ስርአት መፈጠር አለበት ብለዋል። ሰውየው ስለየሽግግር መንግስት መመስረትም አንስተዋል።
ይህ የዶ/ር አረጋዊ አስተያያት ላይ ላዩን ሲታይ በተለይ ስርአቱ ላይ ጭፍን ጥላቻ ላላቸው ወገኖች ግልጽና ቀላል ይመስላል። በደንብ ስናስተውለው ግን ምንም ትርጉም የሌለው፣ ምን መናገር እንደፈለጉ እንኳን የማያመለክት ነው። ዶ/ር አረጋዊ የሚፈልጉት የስርአት ለውጥ ይሁን የገዢውን ፓርቲ ከስልጣን መወገድ በግልጽ አላስቀመጡም።
ዶ/ር አረጋዊ የሚፈልጉት የስርአት ለውጥ እንዲመጣ ከሆነ የሚቃወሙት የኢፌዴሪ ህገመንግስትን ነው። የስርአት ለውጥ ማለት ህገመንግስታዊ ስርአቱን ንዶ በምትኩ ሌላ ስርአት መመስረትን ነው የሚያመለክተው። ዶ/ር አረጋዊ አቋማቸው ይህ ከሆነ እንዲሁ የአንድ ሰሞንን የፖለቲካ ትኩሳት ተከትሎ የስርአት ለውጥ መምጣት አለበት፣ የሽግግር መንግስት ይመስረት እያሉ ፈረንጅ ሃገር ተቀምጠው ስለማያውቁትና ስለማያውቃቸው ህዝብ ከማውራት ይልቅ፣ አሁን ያለውን ህገመንግስታዊ ስርአት – ህገመንግስቱ ወይም ፌደራላዊ ስርአቱ ላይ አለ የሚሉትን ችግርና ሊያስከትል ይችላል ያሉትን አደጋ ከጭፍን ተቃዋሚነት ወጥተው የያዙትን የዶክትርና ማእረግ የሚመጥን ምሁራዊ ትንታኔ መስጠት ይጠበቅባቸው ነበር፤ ይህን ግን አላደረጉም።
እንደሰማሁት ከሆነ እርሳቸው ከህወሃት መስራች ታጋዮች አንዱ ነበሩ። ይህ ከሆነ በኢትዮጵያ የብሄር ጭቆና መኖሩን፣ ይህ ጭቆና ደግሞ ከፍተኛ የሰብአዊና ፖለቲካዊ መብትና ነፃነት ጥሰት መሆኑን ያምናሉ የሚል ግምት አለኝ። እርግጥ አሁን አቋማቸውን ቀይረው ከተስፋ ለዘውድና ተስፋ ለደርግ ቡድኖች ጋር ተቀላቅለው ሃገራችን ተከፋፈለች፣ ልትበታተን ነው ምንትስ ቅብጥርስ የሚለው አመለካከት አራማጀ ሆነው ሊሆን ይችላል።
በኢትዮጵያ የብሄር ጭቆና መኖሩን ይቀበሉም አየቀበሉም፣ የእርሳቸው መቀበል መሬት ላይ ያለውን እውነት አይቀይረውም። ሆኖም የነበረውንና አሁን ያለውን ነባራዊ እውነታ ለእርሳቸውና በስሜት በሚናገሩት ወሬ ውዥንብር ውስጥ ለገቡ የዋሆች ላስታውስ እፈልጋለሁ።
በአሃዳዊው ዘውዳዊና የወታደራዊ ደርግ ስርአት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ህጋዊ እውቅና አልነበራቸውም። ከራሳቸው ቋንቋ ውጭ ሌላ መግባባት የሚያስችላቸው ቋንቋ የሌላቸው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አባላት ፍትህን ጨምሮ የመንግስት አገልግሎት በቋንቋቸው የማግኘት መብት አልነበራቸውም። ህፃናት አፍ በፈቱበትና በብቸኝነት መግባባት በሚችሉበት ቋንቋ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የማግኘት መብት አልነበራቸውም። ይህ በውስጡ ላላለፉ ቀላል ሊመስል ይችላል። ለኖረበት ህዝብ ግን በጣም ፈታኝ ነበር። ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ ለመረዳት፤ የጎንደር ህዝብ ፍርድ ቤት ቀርቦ ጉዳዩ ላይ ምንም በማያውቀው የሶማሊኛ ቋንቋ እንዲሟገት ቢገደድ፣ ህፃናቱ በኦሮሚኛ ቋንቋ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት እንዲማሩ ቢገደዱ የሚገጥማቸውን ፈተና አስቡት። ከአማርኛ ቋንቋ ውጭ የሚናገሩ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዚህ ፈተና ውስጥ የኖሩ መሆኑን ልብ በሉ።
የኑሮ ዘይቤያቸው የሚገለጽበት ባህላቸው ዝቅ ተደርጎ ነበር የሚታየው። ታሪካቸው አሃዳዊውን ስርአት ለማጽናት በሚያስችል ሁኔታ ተዛብቶ ነበር የሚነገረው። ገሚሱም ተደብቆ ነበር። በአጠቃላይ ማንነታቸውን ለመደበቅ የሚያስገድድ ጭቆና ውስጥ ነበር ያለፉት። በቀላሉ ሊደበቅ የማይችለውን ማንነት ለመደበቅ የሚደረግ ጥረት ምን ያህል አስጨናቂ እንደሆነ እናስብ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኢኮኖሚያዊ ጭቆናም ተጭኖባቸው ነበር። በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ላይ በአሃዳዊ ስርአት ስር የተካተቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዝንተ ዓለም በኖሩበት ሃገራቸው የመሬት ባለመብትነት መብታቸውን እንዲያጡ ተደርገዋል። በንጉሰ ነገስቱና መኳንንቱ በሃያና ሰላሳ፣ በመቶዎች ጋሻ የሚለካ ከዚያ ቀደም ሰው ሰፍሮ የሚኖርበት መሬት በርስትነትና ጉልትነት እየተሰጠ ባለሃገሩ ለገባር ጭሰኝነት የተዳረገበት ሁኔታ ነበር።
በአጭሩ በኢትዮጵያ ይህን የመሰለ ብሄራዊ ጭቆና ነበር። ይህ ጭቆና በየአቅጣጫው የብሄራዊ ነፃነት ንቅናቄ አቀጣጥሏል። በመጨረሻዎቹ የወታደራዊ ደርግ የስልጣን ዓመታት እነዚህ በብሄር ተደራጀተው የትጥቅ ትግል ሲያካሂዱ የነበሩ ድርጅቶች ከሃያ በላይ ነበሩ፤ እርግጥ በታጣቂ ታጋይ ብዛትና በትግል ተሳትፏቸው መጠን አንዱ ከሌላው ስለሚለዩ በወቅቱ ሁሉም አይታወቁም ነበር።
የመጨረሻው አሃዳዊ ስርአት የነበረውን ወታደራዊ ደርግ የጣለው ይህ በየአቅጣጫው ሲካሄድ የነበረ የብሄራዊ ነፃነት ትግል ነው።
ከደርግ ውድቀት በኋላ ሃገሪቱ መንታ መንገድ ላይ አረፈች። አንደኛው አቅጣጫ በርካታ ትናንሸ ሃገራት ሆና የመበታተን ሲሆን ሌላኛው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በመቻቻልና በመከባበር በፍቃዳቸው ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በእኩልነት የወሰን ሳይሆን የህዝቦች አንድነት ያላት ሃገር መስርቶ የመኖር መንታ መንገድ ላይ ነበር የቆመችው። በወቅቱ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም ወታደራዊውን ደርግ በተለያየ መንገድ ሲታገሉ የነበሩ ሌሎች የፖለቲካ ሃይሎች ማንም ጣልቃ ሳይገባባቸው መክረው በመከባበርና በእኩልነት ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ የሚኖሩበትን ስርአት መመስረት መረጡ። የኢፌዴሪ ህገመንግስትና በህገመንግስቱ የተመሰረተው የኢፌዴሪ ስርአት የዚህ ወጤት ነው።
እንግዲህ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ይፍረስ የሚሉት ይህን ሃገሪቱ አንድነቷን ጠብቃ እንድትኖር ያስቻለ በብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ፍቃድ የተገነባ ህገመንግስታዊ ስርአት ከሆነ የሚጠብቀን ሌላኛው አማራጭ መበታተን ብቻ ነው።
ዶ/ር አረጋዊ የስርአት ለውጥ የሚሉት ገዢውን ፓርቲ ከስልጣን ማንሳትን የሚመለከት ከሆነ ይህን የማድረግ ስልጣን ያለው ህዝብ ብቻ ሲሆን ይህም የሚከናወነው በምርጫና በምርጫ ብቻ ነው። ሃገሪቱ አንድነቷ እንደተጠበቀ ህዝብ ውክልና የሚሰጠው አካል ስልጣን እንዲይዝ ከተፈለገ ያለው መንገድ ምርጫ ብቻ ነው። ከምርጫ ውጭ የፖለቲካ ቡድኖች ተሰብስበው የሽግግርም ይሁን ሌላ መንግስት መመስረት የሚችሉበት አንዳችም ህገመንግስታዊ አግባብ የለም።
ዶ/ር አረጋዊ የስርአት ለውጥ መምጣት አለበት የሚለውን ከላይ እንዳነሳሁት ስርአቱን መለወጥ ይሁን ገዢውን ፓርቲ በሃይል ማስወገድ በውል ያልታወቀ አቋማቸውን ትክክለኛነት ለማሳየት “ . . . መቶ በመቶ ህዝብ ደግፎናል፣ መቶ በመቶ የፓርላማ ወንበር አሸንፈናል ሲሉ ነበር። አሁን ግን የኢትዮጵያ ህዝብ እየተቃወማቸው ነው። ያ ድጋፍ የት አለ? እንኳን መቶ በመቶ አንድ በመቶም የሚደግፋቸውው የለም” ብለዋል። እናም ከምርጫ ውጭ በሁከት ተወግዶ በሌላ ስርአት መተካት አለበት ባይ ናቸው፤ ዶ/ር አረጋዊ።
መሬት ላይ ያለው እውነታ ዶ/ር አረጋዊ ከሚሉት ጋር አይመሳሰልም። በቅድሚያ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ዶ/ር አረጋዊ እንደሚሉት መቶ በመቶ የህዝብ ድምጽ፣ መቶ በመቶ የፌደራል መንግስት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ አላገኘም። በድምጽ ደረጃ በተለይ በርካታ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነበሩባቸው አካባቢዎች ከአጠቃላይ መራጭ ህዝብ 85 በመቶ ያህል ድምፅ ነው ያገኘው። በተወዳደረባቸው አራት (ኦሮሚያ፣ አማራ፣ የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ ትግራይ) ክልሎች በ50+1 አብላጫ የድምጽ ስርአት አሸንፎ ነው የምክር ቤት መቀመጫዎችን ያገኘው። ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በአፋር፣ በሃራሪ (በከፊል)፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በጋምቤላ ክልላዊ መንግስቶች ኢህአዴግ ጭራሽም አልተወዳደረም። በመሆኑም የምክር ቤቱን መቀመጫ መቶ በመቶ አላሸነፈም።
ዶ/ር አረጋዊ በቅርቡ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎችና በአማራ ክልል በተለይ በሰሜን ጎንደርና በጎጃም ዞኖች አንዳንድ ከተሞች የተቀሰቀሱትን ሁከቶች ገዢው ፓርቲ ወይም የኢፌዴሪ ህገመንግስታዊ ስርአት የአንድ በመቶም የህዝብ ድጋፍ የሌለው ለመሆኑ በአስረጂነት ያቀረቡት።
በቅድሚያ የተቃውሞ ሁከት የተቀሰቀሰው በመላ ሃገሪቱ አይደለም። የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ፣ የአፋር፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ የጋምቤላ፣ የትግራይ ክልሎች አንድም የሁከት ተቃውሞ አልተቀሰቀሰባቸውም። ሁከት በተቀሰቀሰባቸው የአማራና የኦሮሚያ ክልሎችም ቢሆን በሁሉም የየክልሎቹ አካከባቢዎች የሁከት ተቃውሞ ካለመቀስቀሱም ባሻገር፣ ተቃውሞዎቹ አብላጫውን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚወክለውን አርሶ አደር አላካተቱም። ሁከቱ በተቀሰቀሰባቸው ከተሞችም ቢሆን የሁከቱ ተሳታፊዎችና ደጋፊዎች አብላጫ ቁጥር ያላቸው አይደሉም። ምን ግዜም ሁከት ስለሚጎላ ህዝቡ በሙሉ የተሳተፈበት ይመስላል እንጂ አዋኪዎቹ እጅግ በጣም ጥቂቶች ናቸው። አንድን ከተማ ለማወክ የአጠቃላይ ህዝቡ ሁለትና ሶስት በመቶ በቂ መሆኑን ልብ በሉ። ሁከት ለመቀስቀስ አብላጫ መሆን አያስፈልግም። እናም ሁከት መቀስቀሱ በራሱ ሁከቱ በአብላጫ ህዝብ ድጋፍ የተካሄደ መሆኑን አያመለክትም።
ከዚህ በተጨማሪ በኦሮሚያም ሆነ መነሻውን አማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ያደረገው የህዝብ ተቃውሞ የስርአት ለውጥ ጥያቄ የቀረበበት አይደለም። የቀረበው ጥያቄ የህገመንግስታዊ መብት ይከበር እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ነው። ተቃውሞው መልኩን ቀይሮ የዚህ የሁከት ገፅታ የያዘው የኤርትራ መንግስት የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚዎች የዘር ጥላቻን በመቀስቀስ ውዥንብር መንዛት ከጀመሩ በኋላ ነው። የስርአት ለውጥ ጥያቄው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ ሳይሆን የኤርትራ የትርምስ ስትራቴጂ አስፈፃሚ ቡድኖች ጥያቄ ነው። ይህን የስርአት ለውጥ ሁከት የሚቀሰቅሱትን ማህበራዊ ሚዲያዎች በመመለከት መረዳት ይቻላል። ሁሉም ሁከት ቀስቃሾች የኤርትራ መንግስት ወኪሎች ናቸው።
እናም ዶ/ር አረጋዊ ገዢው ፓርቲ የህዝቡ 1 በመቶ እንኳን ድጋፍ የለውም ማለታቸው ፍፁም ስህተትና ምናልባትም አዋኪዎቹን ለማበረታታት ሆን ብለው የተናገሩት ሊሆን ይችላል። ይህ ደግሞ በእርሳቸው የእድሜ ደረጃና ሰፊ የህይወት ተሞክሮ ካለው ሰው የሚጠበቅ አይደለም።
በአጠቃላይ፣ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በቅርቡ በአንዳንድ የሃገሪቱ አካባቢ የተቀሰቀሰውን ሁከት መነሻ በማድረግ የያዙትና ያንፀባረቁት አቋም ግልጽነት የጎደለው፣ ህገመንግስታዊ ስርአቱን በማፍረስ ሃገሪቱን የመበታተን ስትራቴጂ ይዞ ከሚሰራው የኤርትራ መንግስት የትርምስ ጉዳይ አስፈፃሚዎች አቋም ያልተለየ ሃላፊነት የጎደለው ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ታዋቂ ስም ያለው ሁሉ ሃላፊነት የሚሰማው አለመሆኑንም ያሳየ ነው። እናም የኢትዮጵያ ሰላም፣ ዘላቂ ህልውና፣ እድገትና ልማት፣ የህዝቡ የተሻለ ህይወት የሚያሳሰበው ኢትዮጵያዊ፣ ታዋቂ ስም ያለው ሁሉ ቅን እንዳልሆነ ማስተዋል አለበት። ሁሉም እውነተኛ አይደለምና እየመዘነ ይቀበል። ሁሉም ፍሬ ጣፋጭ አይደለም።