ድርቁን በዘላቂነት ለመቋቋም ∙ ∙ ∙

ባለፈው አመት በተከሰተው ኤሊኖ ሳቢያ በተፈጠረው የአየር ፀባይ ለውጥ ሳቢያ ከ10.2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ተዳርገው መቆየታቸው፤ ይህንንም በራሳችን አቅም ተቋቁመን የነበረ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ይህ ክስተት መቃለል በጀመረበት ወቅት የበልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች በድጋሚ በተቀሰቀሰው የዝናብ እጥረት ከአምስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለዕለት ደራሽ አስቸኳይ ዕርዳታ መዳረጋቸውን መንግስት ገልጿል፡፡

በበልግ ወቅት የሚጠበቀው የዝናብ ስርጭት መቀነሱም በበልግ ዝናብ አምራች የሆኑ አካባቢዎች የምርት መቀነስ እንደሚጠብቃቸው በመገመቱ፣ በድርቅ የተመቱትን አካባቢዎች ይበልጥ ሥጋት ውስጥ እንደከተታቸው ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት የወጡ ሪፖርቶች ይፋ አድርገዋል፡፡ በዚህ ሳቢያም በድርቅ የተመቱ የአርብቶ አደር አካባቢዎች የማገገም ተስፋቸውን ጥያቄ ውስጥ እንደከተተው የሚያመለክቱት ደግሞ የብሔራዊ ሚትዮሮሎጂ የትንበያ መረጃዎች ናቸው፡፡ 

በበልግ ዝናብ በመታገዝ ከሚያመርቱ አካባቢዎች መካከል የደቡብና የደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ክፍሎች በአብዛኛውም የደቡብ ሶማሌ ክልል፣ በኦሮሚያ የቦረና ቆላማ አካባቢዎች፣ የጉጂና የባሌ ዞኖች እንዲሁም የደቡብና የአፋር ክልሎች እንደ አዲስ ባገረሸው ድርቅ ተጎጂ መሆናቸው ሲታወቅ፣ ከየካቲት አጋማሽ እስከ ግንቦት ወር በሚኖረው የበልግ ወቅት የሚያገኙት ዝናብ ደካማ እንደሚሆን በመገመቱ የማገገም ዕድላቸውን አሳሳቢ ያደረገው ስለመሆኑም መረጃዎቹ አመልክተዋል፡፡

በእነዚህ አካባቢዎች እንደሚኖር የሚጠበቀው ደካማ የዝናብ ሥርጭት ከሚጠበቀው እና መደበኛ ከነበረው ዝናብም ያነሰ እንደሚሆን የሚያመላክቱት መረጃዎች ለበልግ ሰብሎች ታስቦ የሚደረገውን የመሬት ዝግጅትም ሆነ የሰብል መዝራት ተግባር በእጅጉ እንደሚጎዳው ይጠቅሳሉ፡፡ የውኃ አቅርቦትንና እርጥበትን በመቀነስ በሚያሳድረው ተፅዕኖ ሳቢያም ዜጎች ለምግብ እጥረትና ለተመጣጠነ ምግብ እጦት እንዲዳረጉ ምክንያት በመሆኑ፣ ቀድሞውንም በድርቅ የተጎዱትን ይበልጥ ጉዳት ላይ እንደሚጥላቸው ሥጋት ፈጥሯል፡፡

ብሔራዊ የሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሚያስተባብራቸው 30 ያህል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎችና ሌሎች ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች የሚሳተፉበት ጥምረት፣  በጥር ወር መጀመሪያ አካባቢ ይፋ ባደረጉት ሰነድ መሠረት ለድርቁ መቋቋሚያ ከ948 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ገልጿል፡፡ አሁን በአስቸኳይና በዘላቂነት ይህን እና ባልተለመደ ሁኔታ አከታትሎ የመጣብንን ድርቅ እንዴት መቋቋም ይቻላል? የሚለው ጥያቄ የሁሉም ነውና ጊዚያዊዎቹንም  ሆነ ዘላቂ ከሚሆኑ መፍትሄዎች ጥቂቶቹን ማንሳትና የጋራ ግንዛቤ መፍጠር ጊዜው የሚጠይቀን ጉዳይ ነው።

መንግስት በአርብቶ አደሩ አካባቢ የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም በ47 ሚሊዮን ብር ወጪ የመጀመሪያ ዙር እርዳታ በማቅረብ ጊዚያዊውን መፍትሄ መስጠት የጀመረ መሆኑን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ይፋ አድርጓል። ኮሚሽኑ ባለፈው ዓመት 10 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች እርዳታ ሲያገኙ መቆየታቸውን አስታውሶ በተያዘው ዓመት ደግሞ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎችን እየደገፈ መሆኑንም ጨምሮ  ገልጿል። በእርግጥ የዘንድሮው ዓመት የተረጂዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር በ44 በመቶ ዝቅ ያለ መሆኑ አንድ ተስፋ ነው ።

 

መንግስት ያለፈውን ልምድ በመጠቀም ለተረጂዎቹ ከሚያስፈልገው 700 ሺህ ዶላር አጠቃላይ በጀት በራሱና በአጋሮቹ ለመሸፈን እየተንቀሳቀስኩ ነው ማለቱ ለጉዳዩ የሰጠውን ትኩረት በአንድ በኩል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከውጭ እርዳታ ጥገኝነት መላቀቅ ያስቻለ ኢኮኖሚ እየተገነባ መሆኑን የሚያመላክት ነው።

 

በዚህም መንግስት ለአዲስ ተረጂዎች የሚውል 47 ሚሊዮን ብር አውጥቶ የምግብ እህል፣ አልሚ ምግቦችና ዘይት እያከፋፈለ ሲሆን፤ በጥቅሉ 75 ሚሊዮን ብር ወጪ ሆኖ ለተረጂዎቹ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑ በእርግጥም ድርቅን መቋቋም የሚያስችል ኢኮኖሚ እየተገነባ ለመሆኑ ሁነኛ ማሳያ ነው።

 

መንግስት እንደ ባለፈው ዓመት ሁሉ ዘንድሮም ለተረጂዎች የሚያስፈልጉትን የምግብ እህል፣ አልሚ ምግብና ዘይትን ጨምሮ ሌሎችንም ቁሳቁሶች አቅርቧል። ለእንሰሳት ኃብቱም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን መረጃዎች እያመላከቱ ነው።   

 

የአሁኑን ከባለፈው አመት ለየት የሚያደርገው የድርቁ አጠቃላይ አዝማሚያ የእንስሳት ህይወትን በስፋት ሊቀጥፍ የሚችል መሆኑ ነው። ይህን ችግር ለመቅረፍም የመኖ አቅርቦት እየተዘጋጀ ሲሆን እንስሳቱም ለገበያ እንዲቀርቡ እየተደረገ መሆኑን መረጃዎቹ ጨምረው ገልጸዋል። በተለይ ደግሞ እንስሳቱን መኖ ወዳለባቸው አካባቢዎች ከማጓጓዝ ጀምሮ መኖ ያላቸው ክልሎች እና አጎራባች ዞኖች የህዝብ ለህዝብ ድጋፍ በማድረግ ድርቁን በጊዚያዊነት ለመቋቋም እየተደረገ ያለው ጥረት እጅግ የሚያበረታ እና የሚያነቃ ነው።

 

ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችና በተሞክሮነት ሊወሰዱ የሚገባቸው ተግባራት እየተከናወኑ ካሉባቸው አካባቢዎች ደግሞ ኦሮሚያ በቀዳሚነት ይጠቀሳል። የኦሮሚያ ክልል ባሌና ምዕራብ አርሲ ዞኖችን ስነ-ምህዳር ለመጠበቅ ሲተገበር የቆየው ሼር የተሰኘ ፕሮጀክት 12 ሚሊዮን የአካባቢ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማደረጉን ሰሞኑን ይፋ አድርጓል።

 

የፕሮጀክቱ ዓላማ እየጨመረ የመጣው የህዝብ ብዛት በባሌ አካባቢ ስነ-ምህዳር ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በጥናት በመለየት የመፍትሄ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ማድረግና የአካባቢውን ነዋሪዎች የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ነው። ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ከአውሮፓ ኅብረት የተገኘ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ የተመደበ ሲሆን በ40 ወራት ለማጠናቀቅ ታቅዷል።

 

ፋርም አፍሪካ፣ ኤስ ኦ ኤስ ሳህል፣ ዓለም አቀፉ የውኃ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት፣ ፍራንክፈርት ዞሎጂካል ሶሳይቲና ፖፑሌሽን ሄልዝ ኢንቫይሮመንት ኢትዮጵያ የተሰኙ ተቋማት ፕሮጀክቱን በጋራ ከውነውታል። የውኃ አጠቃቀምና የስነ-ምህዳር አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ፣ የእንስሳት ኃብት፣ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት፣ የአካባቢውን ነዋሪዎች የገቢ ምንጭ የሚያሳድጉ ተግባራትን ማከናወን በፕሮጀክቱ ጥናት የተካተቱ ጉዳዮች መሆናቸው ይፋ በሆነው መረጃ ተመልክቷል። ፕሮጀክቱ ሲተገበር በቆየባቸው ዓመታት የአካባቢውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤቶች ተገኝተዋል። 12 ሚሊዮን ዜጎችን የንጹህ መጠጥ ውኃና የመስኖ አገልግሎት ተጠቃሚ በማድረግ ድርቅ የማያሰጋው የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ተችሏል።

በአጠቃላይ በፕሮጀክቱ ከ873 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ቀጥተኛ ተጠቃሚ ሲሆኑ 12 ሚሊዮን ደግሞ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ተጠቃሚ ሆነዋል። ይህ ደግሞ ወደሌሎችም ድርቅ የሚያጠቃቸው አካባቢዎች ላይ መሄድ የሚገባው ተሞክሮ ነው።

 

ሌላውና እንዲህ ያለውን የድርቅ አደጋ በዘላቂነት ለመቋቋምና ለመቀነስ በአየር ትንበያ ላይ ያተኮረ ስራ ማከናወን እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ልሂቃን ይመክራሉ። የኢጋድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ "በአፍሪካ ቀንድ በ2016/17 ለደረሰው አስከፊ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ መስጠት" በሚል መሪ ሃሳብ አዲስ አበባ ላይ ባደረገው ጉባዔ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) አባል አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ አሁን እያደረጉት ካለው እንቅስቃሴ በተጨማሪ የአየር ትንበያን መሰረት በማድርግ መስራት ይኖርባቸዋል የሚለው ሃሳብ ገኖ የወጣውም ስለዚህና የልሂቃኑ ምክረ ሃሳብ ትክክል ስለሆነ ነው።

 

በ45ኛው የኢጋድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ ንግግር ያደረጉት በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ተወካይ ሚስ ሜካህ ሽሬትሳ እንዳሉት በየጊዜው የሚከሰተው አስከፊ ድርቅ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል። የኢጋድ አባል አገራት ይህን ችግር ለመቀነስ ከየአገራቱ የሚቲዎሮሎጂ ድርጅቶች የሚሰጠውን መረጃ በመቀበል ከባለ ድርሻ አካላት ጋር መስራት ይኖርባቸዋል ብለው የነበረ መሆኑ ይታወሳል። አባል አገራቱ ኢትዮጵያ በሁለት ዓመታት ውስጥ በድርቅ የተጎዱ ዜጎቿን ቁጥር ከ10 ሚሊዮን ወደ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን የቀነሰችበትን ልምድ መውሰድ አለባቸው ሲሉ መምከራቸው ደግሞ በትክክለኛ ፖሊሲ ተቃኝተን እየተጓዝን መሆኑን የሚያጠይቅ ነው። (መረጃዎች እንደሚያሳዩት በ2010/11 በአፍሪካ ቀንድ 13 ሚሊዮን ዜጎች በድርቅ የተጠቁ ሲሆን ይህ ቁጥር በማሻቀብ በ2016/17 ወደ 17 ሚሊዮን ደርሷል) ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስት ከብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ጋር በቅርበት እየሰራ በመሆኑ ሳይወሰን እስከ ታችኛው መዋቅር ድርስ በማውረድም ከኤጀንሲው የሚገኘውን መረጃ ተግባራዊ ማድረግ ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም ያስችለናል።

 

 

ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም የሚያስችል አንድ ተሞክሮ ደግሞ ከወደትግራይ እናምጣ። የአላማጣ እርሻ ምርምር ማእከል ያላመዳቸውን 81 የሰብልና የጥራፍሬ ዝርያዎች  በማላመድ በክልሉ ለሚገኙት  አርሶ አደሮች ባሳለፍነው ወር መጀመሪያ አካባቢ አሰራጭቷል።  ከተሰራጩት የሰብል ዝርያዎች መካከል በሄክታር እስከ 35 ኩንታል ምርት የሚሰጡ የጤፍና እስከ 70 ኩንታል ምርት የሚሰጡ የስንዴና የማሽላ ዝርያዎች ሲገኙበት፤  በሄክታር እስከ 80 ኩንታል ምርት የሚሰጡ የበቆሎ ዝሪያዎችን በማላመድ ለአርሶ አደሩ እንዲሰራጭ መደረጉን የክልሉ የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ገልጿል፡፡ ሦስት አይነት የደቆቆ ዘሮችን ጨምሮ 19 የአተር፣ የቡና፣ የፓፓየ፣ የቀይና ነጭ ሽንኩርት፣ የቲማቲምና የቃሪያ ምርጥ ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት የአካበቢው አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ላይ ነው። ማእከሉ ባለፉት አራት አመታት ባካሄዳቸው የምርምርና የማላመድ ስራዎች የዞኑ አርሶ አደሮች የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ በማስቻል ድርሻውን መወጣቱ የሚያበረታታና ሌሎችም ሊወስዱት የሚገባ ተሞክሮ ይሆናል። በግብርናው ዘርፍ የምርምር ውጤቶችን በማስፋፋት በአካባቢው አርሶ አደሮች መካከል የሚታየውን የምርታማነት ልዩነት ማጥበብ ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም ያስችላል።

 

ምርጥ ዘሮችን እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማላመድ ብቻ ሳይሆን የገበያ ትስስር መፍጠርም ድርቅን በዘለቄታዊነት ለመቋቋም የሚያስችል መሆኑንም ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።   የተደራጀና የተቀናጀ የባለሙያ ድጋፍ ከዝግጅት ጀምሮ እስከ ምርት ማሰባሰብና ግብይት ድረስ ለአርሶ አደሩ  መስጠት  ያስፈልጋል ፡፡

 

ሁሉም አርሶ አደር በአንድ ወቅት ምርቱን ወደ ገበያ ሲያቀርብና የአቅርቦት መጠኑ ከፍላጎቱ ሲበልጥ የዋጋ መውረድ ስለሚያጋጥም የአርሶ አደሩን ተነሳሽነት በመቀነስ ለምርት ክፍተት ይዳርጋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት አርሶ አደሩ በኩታገጠም ተደራጅቶ የተለያየ ምርት እንዲያመርት ከማድረግ ባለፈ ከማህበራት ጋር በመቀናጀት ገበያ የማፈላለግ ስራ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ይህ አሰራር የድርቁን አደጋ በዘላቂነት ከመፍታት ባለፈ ለዘላቂ ልማታችንም የሚኖረው አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለምና የተለየ ትኩረትን ልንቸረው ይገባል።