ከደቡብ ሱዳን ሕዝብ ግማሽ ያክሉ የምግብ እጥረት ሥጋት ተጋረጠበት

ከደቡብ ሱዳን ሕዝብ ግማሽ ያክሉ የምግብ እጥረት ሥጋት እንደተጋረጠበት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ አስታወቀ።

በደቡብ ሱዳን የቢሮው ቃል-አቀባይ ፍራንክ ንያካይሩ እንደገለጹት፤ 5ነጥብ2 ሚሊዮን ደቡብ ሱዳናውያን የምግብ እጥረት ገጥሟቸዋል፡፡

ቁጥሩ 4ነጥብ9 ሚሊዮን ደቡብ ሱዳናውያንን፣ እንዲሁም፣ ላለፉት አምስት ዓመታት በአገሪቱ የተጠለሉ 260 ሺህ የሱዳን፤ ኮንጎ እና ኢትዮጵያ ስደተኞችን ያካትታል።

የደረቅ ወቅቶች መራዘም፤ጎርፍ እና የከባቢ አየር ለውጥ የአገሪቱን የእርሻ ሥራ እንዳስተጓጎለው የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

ማባሪያ ያጣው የአገሪቱ ግጭት ለተፈጠረው የምግብ እጥረት ቀውስ አስተዋጽዖ ማበርከቱም ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ኢዩጊን ኦውሱ ግጭት፤ የኤኮኖሚ ቀውስ እና የከባቢ አየር ለውጥ ተባብረው የደቡብ ሱዳንን ሰብዓዊ ይዞታ በፍጥነት እንዲያሽቆለቁል ማድረጋቸውን አስገንዝበዋል።

የእርዳታ ድርጅቶች በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓመተ ምህረት ለተቸገሩ ደቡብ ሱዳናውያን ምግብ እና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች ለማቅረብ 1ነጥብ6 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልገናል ብለዋል።