ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር 70 የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያገናኘዉ የመጀመሪያዉ መድረክ

በሃገራችን ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች አለመኖራቸዉና በቂ አሳታፊ የፖለቲካ ድባብ አለመኖሩ በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመፍጠር የተደረገዉ ጥረት ሁሉ እዚህ ግባ የሚባል ውጤት ማስመዝገብ ተስኖት ዘመናትን አሳልፏል፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት ፓርቲዎቹ ቁጥራቸዉ ከልክ በላይ ከመሆኑም ባለፈ በሳል፣ ግልጽና ጥርት ያለ የፖለቲካ አደረጃጀት፣ ርዕዮተአለምና አቅጣጫ የሌላቸው በመሆኑ አካሄዳቸው ለህዝብና ሃገር የሚጠቅም ፍሬ ከማበርከት ይልቅ ህዝብን ለትርምስ፤ ሀገርን ደግሞ ለብጥብጥ ሲዳርግ ቆይቷል፡፡  በሌላ በኩል እነዚህ ፓርቲዎች በመንግስት በኩል ነጻና ግልጽ የውይይት መድረክ ስላልተመቻቸላቸው እንዲሁም በራሳቸው ችግሮች ምክንያት ባለተደራጀና በተበታተነ መልኩ ሲታገሉ ነበር፡፡ አንደኛው ጎራ በሃገር ውስጥ ሆኖ ከገዢው ፓርቲና እርስ በርሱ የሚናቆር፤ ሌላኛው ወገን ከባህር ማዶ ሆኖ የተለያዩ ብዙሃን መገናኛዎችን በመጠቀም የቆመለትን አላማ የሚሰብክ ሌላኛው ደግሞ የትጥቅ ትግልን ብቸኛ አማራጭ  ያደረገ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሃገራው ገብተው እንዲወያዩና ሰላማዊ ትግል እንዲያደርጉ ባስተላለፉት ጥሪ መሰረት ሁሉም ፓርቲዎች ለዶክተር አቢይ ጥሪ ምላሽ በመስጠት ወደ ሃገራቸው ገብተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እና ባጠቃላይ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦና ተመካክሮ እንደሚሰራ በገቡት ቃል መሰረት ባለፈው ማክሰኞ ህዳር 18 ቀን ወደ ሰባ ከሚጠጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የመጀመርያ ደረጃ ውይይት ማድረግ የጀመሩ ሲሆን የውይይቱን በይፋ መከፈትም አብስረዋል፡፡ ይህ ጽሁፍም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተመራውን የፖለቲካ ፓርቲዎች የመጀመርያ ደረጃ ውይይት ዓላማ፣ ሂደት፣ጭብጥ፣ ትኩረትና ግብ ላይ ያጠነጥናል፡፡

ባለፉት ጊዜያት ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣውን ለውጥ እና ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በቅርበት ማወቅ፣ መምራትና ሃሳብ መስጠት እንፈልጋለን የሚሉ ሰፋፊ ጥያቄዎች በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲነሱ መቆየታቸው የዚህ ውይይት መነሻ ሃሳብ እንደሆነ ዶክተር አቢይ ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ምክንያቶች ውይይቱ በፍጥነት እንዳይጀመር እንዳደረጉ ገልጸው ምክንያቶቹንም ዘርዝረዋል፡፡

ከለውጡ በኋላ በተቃውሞ ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች (የታጠቁም ያልታጠቁም) በተለያየ አለም ተበታትነው ስለሚገኙ በተሟላ ሁኔታ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ለመጠበቅ ሲባል፤ በርካታ ሊሻሻሉ የሚገባቸው አዋጆችና አሰራሮች ስለነበሩ እነሱን መነካካት እና የፍትህ ሪፎርሙን ማሳለጥ ያስፈልግ ስለነበር፤ የምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አይደለም ተብሎ ስለሚታማ እሱን ለማሻሻል ቢያንስ የመጀመሪያ እርምጃ መውሰድ ስለሚገባ እና መሰል ስራዎች ቀደም ብለው መሰራት ስላለባቸው ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ አሁን የተጀመረውና በየደረጃው የሚደረገው ውይይት ፍሬያማ እንዲሆን ሁሉም የውይይቱ ተሳታፊዎች ትኩረት መስጠት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡ መሰል ውይይቶች ለፖለቲካ ፓርቲዎች አዲስ ባይሆኑም ውጤታማ ስላልነበሩ ፍሬ መስጠት ግን አልቻሉም ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ተወያዮቹ ውይይቱን የሚጀምሩት ተወያይተው፣ ተግባብተው፣ ሃሳብ ተቀያይረውና የጋራ ነገር ይዘው ለመውጣት በማለም አለመሆኑ ውይይቱን ስር እንደሌለው ችግኝ እንዲሆን አድርጎታልም ብለዋል፡፡ በመሆኑም አሁን የተጀመረው  ውይይት የነበርንበት የፖለቲካ ልምምድ ያስገኘውን ውጤትና ድክመት በውል የምንለይበት፤ ከድክመቶቻችን ተምረን ወደ ላቀ ደረጃ ለመሸጋገር የሚያስችል ሁኔታ ላይ መሆናችንን እያረጋገጥን የምንሄድበት ይሆናል ብለዋል፡፡

ሃገር ያለ ሰው/የፖለቲካ ፓርቲ መኖር የምትችል ሲሆን ሰው ግን ያለ ሃገር መኖር አይቻለውምና ሃገር በማፍረስ ተግባር ላይ የተሰማራና ለሃገር መኖር የሚፈልግ ፓርቲ ወይም ፖለቲካዊ እሳቤ ያለው ማንኛውም አካል ዋና መሰረቱ ወይም ስሩ እንደተቆረጠ ችግኝ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም መንግስትን ጨምሮ ሁሉም ፓርቲዎች የምሰራው ስራ መቀመጫችንን/ሃገራችንን የማያፈርስ መሆን ይኖርበታል ብለው እያፈረስን ከሆነ ግን ፖለቲካው አብቦ ፍሬ ሊሰጥ አይችልም ሲሉ ተናረዋል፡፡

የውይይቱ አላማዎችም በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚካሄደው ውይይት እንዴት ይካሄድ? ምን መልክ ይኑረው? በሚለው ሃሳብ ላይ ለመግባባት፤ የውይይቱ ጉዳዮችና የሚፈቱበት መንገድ ላይ የመነሻ ሃሳብ ለማቅረብ፤ ውይይቱ እንዴት፣ በማን እና መቼ ይመራ? ምን መነሻ ሃሳብ ይኑሩት? በሚለው ሃሳብ ላይ ውይይት ተደርጎ አቅጣጫ ማስቀመጥና የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት በይፋ መጀመሩን ለመግለጽና ከዚህ በኋላ የምርጫ ቦርድ በሚያስቀምጠው መርሃ ግብር መሰረት የውይይትና የፖለቲካ ባህላችንን ሊያሳድጉ የሚችሉ መድረኮችን መፍጠር ናቸው፡፡                                                     

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ውይይቱን ለመጀመር እንዲቻል የመንደርደሪያ ሃሳቦችንም አነስተው ማብራሪያ ሰጥተውባቸዋል፡፡

ከመንደርደሪያ ሃሳቦቹ ትኩረት ማካከልም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአንድ ሀገርና ህዝብ የሚሰሩ እስከሆነ ድረስ መወያየት ግዴታ መሆኑ ተሰምሮበታል፡፡ በርካታ አመታትን በፖለቲካው ውስጥ የቆዩና የፖለቲካ ሳይንስ የተማሩ በርካታ ፖለቲከኞች ቢኖሩም ሁሉም መገንዘብ ያለባቸው ሃገራችን ፖለቲካን ሀ ብላ የምትማር መሆኗን ነው፡፡ ፖለቲካው ውስጥ ነበርኩበት፤ አውቀዋለሁ የሚል አስተሳሰብ ለመማማር የሚደረገውን ጥረት ያደናቅፈዋል፡፡ በፓርቲዎቹ መካከል የርዕዮተዓለም፣ የፖሊሲ፣ የስትራቴጂና የስልት ልዩነት አለ ወይ የሚለው በውይይት ወቅት የሚታይ ቢሆንም ልዩነቱ ከህዝብና ከሃገር ስለማይበልጡ በህዝብና በሃገር ጥላ ስር ሆነን በመወያየት የጋራ ሃሳብ መያዝ ይገባል፡፡

ሰው ሁሉ ጠቃሚ ነውና ሃሳቡ በሙሉ ይደመጣል፤ ከተደመጠ በኋላ ገዢው ሃሳብ ስራ ላይ ይውላል፡፡ የምርጫ ውጤትን ጨምሮ በሌሎች ነገሮች ላይ መግባባት የሚቻለው በጨዋታ ህጉና በዳኞች ላይ እምነት ሲፈጠር በመሆኑ ህጉንና ዳኛውን እኛው በጋራ እናስቀምጣለን በዚያ ህግ እንመራለን፡፡ በመሆኑም ይህን ህግ የሚጥስ አካሄድ ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡ የተቀራረበ ሃሳብ ያላቸው ፓርቲዎች በመቻቻል ቢሰባሰቡና የፓርቲዎችን ቁጥር ወደ አምስት ወይ ስድስት ዝቅ ማድረግ ብንችል ጥሩ ይሆናል፡፡ ሀገር፣ ህዝብና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት የጋራ አላማችን ይሆናል፡፡

 

ዉይይቱ በዋናነት የችግሮቹን አይነቶች አንድ በአንድ መለየትና ዘርዝሮ በማስቀመጥ  አጣዳፊና ጫና ፈጣሪ የሚባሉትን መለየት መቼና በምን መንገድ ይፈቱ የሚለዉን በማየትና   ከስምምነት የተደረሰባቸውን ጉዳዮች ለህዝብ ይፋ የማድረግ አቅጣጫን ይከተላል፡፡ ህግና ህገ መንግስትን ማክበር  -ባለው ህግ መገዛት ያስፈልጋል፤ የተመቸንን ህግ ወስደን ያለተመቸንን እየጣልን መጓዝ  አንችልም፤ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡እንዲሁም ለብዙሃን ሃሳብ መገዛት/ማመቻመች  ሁለት የተለያዩ ሃሳቦች ቢቀርቡ ከሁለቱም የተለየና የተሻለ አማራጭ ይዞ መቅረብና ውይይቱ በሶስት ደረጃዎች ተከፋፍሎ ቢካሄድ የሚል ሃሳብ ከጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ቀርቧል፡፡  

በመጀመሪያ ደረጃ ለውይይት አመቺ መድረክ መፍጠርና ለዚህም መድረኩን መክፈት፤የስነምግባር ሰነድ ማዘጋጀት ሰው ሳይሞትና ሳይቆስል በውይይት ብቻ ፖለቲካን መምራት መቻል ወሳኝ መሆኑንም አዉስተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የዴሞክራሲ ተቋም/ባህል ግንባታ እንዲሁም ከምርጫ በኋላ ዘላቂና የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት መፍጠር ያሻል፡፡

ጠቅላይ ምኒስትሩ ውይይቶችን በየደረጃው ማካሄድ ያስፈለገበት ምክንያት በሃገሪቱ ያለው ያለመረጋጋት፤ተቋማት ስምና ሃላፊ ቢፈጠርላቸውም ከላይ እስከታች ተሰናስሎ ለማደራጀት ጊዜ ስለሚያስፈልጋቸውና የተሳካ ምርጫ ከተደረገ ህዝባዊ አመኔታ ያለው መንግስት ማዋቀር ስለሚቻልና በዚህ ሃይል የሚመራ ማንኛውም ለውጥ ተዓማኒነት ያለው ስለሚሆን ነዉ ብለዋል፡፡                       

በሁሉም ደረጃዎች የሚከናወኑ ውይይቶች 4 ዋና ዋና ዓላማዎች አሏቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ህጋዊና ከግጭት ስጋት ነጻ  በሆነ ድባብ በውይይትና ምክክር እንዲካሄድ ማድረግ፤በመላው ሃገሪቱ ሊኖር የሚገባውን የሰላምና የመረጋጋት ሁኔታ ፓርቲዎች በሃላፊነት የሚመሩት እንዲሆን ማስቻል፤ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰለጠነ አኳኋን በውይይትና ምክክር ሃሳባቸውን መቀያየር እንዲችሉ ማድረግ እንዲሁም ለቀጣይ ደረጃዎች መልካም የሆነ መሰረት መጣል ናቸው፡፡

የውይይቱ ዋና ዋና ጭብጦች ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በውይይቱ እንዲሳተፉ በሁሉም አይነት መንገድ ጥሪ ማስተላለፍ፤ ቀጣይ ውይይቶች የሚመሩበት መንገድ፣ አካሄድና የጊዜ ሰሌዳ ላይ መስማማት በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጂም ጊዜ ሊፈቱ የሚችሉ ጉዳዮችን የማየትና የትኞቹ ጉዳዮች በየትኛው ዙር እንደሚወድቁ ተስማምቶ በዚህ አግባብ ለመስራት እድል መፍጠር የሚሉትን አካተዋል፡፡ እንዲሁም በቀደምት ጊዜያት ፍሬያማ ካልነበሩ ውይይቶች ለመማማር የሚያግዙ ካሉ እነሱን እያዩ እንዳይደገሙ ማድረግ፤የውይይቱ አጠቃላይ ሂደት የሚመራበት ዝርዝር የስነ ምግባር ሰነድ በምርጫ ቦርድ በውይይቱ ተሳታፊዎች ውይይትና ምክክር ማዘጋጀት ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ኢ-ዴሞክራሲያዊና ከተቀመጠው ስነ ምግባር ውጭ ከሆነ መንግስት እርምጃ የሚወስድ መሆኑም በትኩረት ተወስቷል፡፡

ከውይይቱ የሚጠበቁ ውጤቶችም ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማከናወን ቁርጠኛ አቋም የያዘና ያንን ለማከናወን የሚረባረቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያካተተ፤ በእነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውሳኔ ወይም ድክመት ምክንያት ከምርጫ በኋላ የሰው ህይወት እንዳይጠፋና ንብረት እንዳይወድም በከፍተኛ ጥንቃቄ መስራት ፤ በምርጫ የሚሳተፉ አመራሮች፣ እጩዎች፣ደጋፊዎች፣ ታዛቢዎችና አባላት ላይ ከአሁኑ የአቅም ግንባታ ስራ መስራት ፤ በህግ ማሻሻያው ላይ ዘርዘር ያሉ ጉዳዮች ታይተው ያንን ለመመለስ በሚደረገው ሂደት ምርጫው ስኬታማ ድምዳሜ እንዲኖረው ማድረግ ጥሩ የፖለቲካ ባህል እንዲፈጠር እድል መፍጠር ናቸዉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከላይ በተጠቀሱ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን አስተያየቶችም ተሰጥተዋል፡፡

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ፓርቲ አባል ዶክተር አረጋዊ በርሄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባነሷቸው ሃሳቦችና በውይይት መንደርደሪያ ጋር በአመዛኙ እንደሚስማሙ ገልጸው ለስርዓት ግንባታ ከፍተኛ ትኩረት ቢሰጥ ብለው ጠይቀዋል፡፡ ስርዓቱ ከተበጀና ሃዲዱ ከተዘረጋ ምርጫውም፣ የፌደራል ስርዓቱም ሌሎችም ጥያቄዎች በሰከነና የህግ የበላይነት ባለበት ሂደት ሊጓዝ ስለሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

ችግሩ የመንግስት ብቻ አልነበረም እኛ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም  70 እና 80 ሆነን በተንዛዛ መልኩ የምናስተላልፈው መልዕክት ህዝብን ከማተራመስ ውጭ ህዝቡ እንዲያውቅ፣ እንዲጠይቅና እንዲቆጣጠረን እድል አልሰጠውም፡፡ ስለዚህ ተፎካካሪ ፓርቲዎችበ3 ውይም በ4 ፓርቲ ብንጠቃለል የሚል አስተያየትም ሰጥተዋል፡፡

የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው መንግስት ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲኖር መፈለጉ በጣም ጠቃሚና አስፈላጊ ጉዳይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ እስካሁን ድረስ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንቅፋት የነበረው መንግስት ነበር፤ አሁን መንግስት ችግር አይሆንምና ጥሩ ነገር ነው፡፡ ውይይቶቹም በ3 ደረጃዎች ቢከናወኑ በሚል በዶክተር አብይ የቀረበዉን ሃሳብ እኔም እጋራዋለሁ ብለዋል፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አመራር አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ ሲሆኑ በሃገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ምን መሆን አለበት በሚል ለመወያት በመንግስት በኩል ጥሪ መደረጉ ለፓርቲዎች ክብር የሰጠ በመሆኑ ጥሩ ነው ብለዋል፡፡ ውይይቱ በቀጣይ ምርጫ ላይ ብቻ መታጠር እንደሌለበትም አቶ ክርስቲያን ተናግረዋል፡፡ ከምርጫው በፊት መተማመን፣ መደማመጥና መከባበር ያስፈልጋል፡፡ ለመተማመን ደግሞ መተማመኛ የሆኑ ነገሮች ያስፈልጋሉ፡፡ ለምሳሌ በስራ ላይ ያለው ህገ መንግስት ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በእኩል ህገ መንግስቴ ብለው እንዲቀበሉትና እኩል ለዚህ ህገ መንግስት ጥብቅና እንዲቆሙለት ያስፈልጋል፡፡ በህገመንግስት ጉዳይ ላይ ውይይት አለማድረግ ኢ ፍትሃዊነት ነው ብለን እናምናለን ብለዋል፡፡ ከፍትህ አንጻር ያለፈውን እያነሳን መቆዘም ባይኖርብንም በስማቸው መጠራት ያለባቸው ወንጀሎችና ወንጀለኞችን በስማቸው መጥራት ያስፈልጋል፡፡ ፍትህ ቅድሚያ መስፈን አለበት፡፡ የካሳ እቅድ ተዘጋጅቶ እርቅ መውረድ አለበት ብለዋል፡፡ የህዝብ ቆጠራ ከምርጫው በፊት መከናወን እንዳለበትም እንዲሁ፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የፓርቲያውን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ህዝብ ጠቃሚ ለሆኑ ጉዳዮች ቅድሚያ ቢሰጡ ብለው አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡

ደክተር አቢይም ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ “ለተቋማት ግንባታ ቅድሚያ ይሰጥ ብለው ዶክተር አረጋዊ ያነሱትን እኛም ቅድሚያ ሰጥተን እየሰራንበት ነው፡፡ እስካሁን በዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ ላይ ምን ሰራችሁ ብላችሁ ከጠየቃችሁኝ በዝርዝር ልናቀርበው እንችላለን ብለዋል፡፡ ቅድሚያ ለሰላም፣ መረጋጋት እና ውይይት እንሰጣለን፤የኛም እምነት ፓርቲዎች ተቀራርበውና ግንባር ፈጥረው 2 እና 3 ሆነው ቢወያዩ ጥሩ ዉጤት ማምጣት ይቻላል የሚል ነው” ብለዋል፡፡  

ከአቶ ክርስቲያን ለተነሳውም ጥያቄ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ “ህገ መንግስቱ ላይ እንወያያለን ተወያይተን ከተግባባን እናሻሽለዋለን፡፡ ካልተግባባን ህዝቡ ይወስናል፡፡ የህዝብና ቤት ቆጠራ ጸድቆ ስራው እየተጀመረ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ከምርጫ በፊት ይካሄዳል፡፡ በተመሳሳይም የእርቁ ጉዳይ የእርቅ ኮሚሽን ካቢኔ አጽድቆት ፤ መነሻ ሃሳብ ለፓርላማ ልኳል፡፡ ይህም በሚዲያ በስፋት ተገልጿል፡፡ አቶ ክርስቲያን ወንጀልና ወንጀለኛን በስማቸው እንጥራቸው ብለው ላቀረቡት ሃሳብ በርካታ ባለቤት የሌላቸው/ያልተገኘላቸው በደሎች አግኝተናል” ሲሉ አጠቃለዋል፡፡