ናይጄሪያ በደቡብ አፍሪካ ለሚገኙ የሀገሪቱ ዜጎች ነፃ የአውሮፕላን ትኬት አቀረበች

በደቡብ አፍሪካ በውጭ ሀገራት ዜጎች ላይ ያተኮረ ጥቃት መቀስቀሱን ተክትሎ ናይጀሪያ በሀገሪቱ በመኖርና በመስራት ላይ የሚገኙ ዜጎች ወደ ናይጄሪያ ይመለሱ ዘንድ  ነፃ የአውሮፕላን ትኬት አቅርባለች ፡፡

የናይጄሪያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በትዊተር ገፁ እንዳስታወቀው ፤ከደቡብ አፍሪካ ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ዜጎች የነፃ የአውሮፕላን ጉዞ ትኬትን ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡

የሰላም አየርመንገድ ሃላፊ አለን ኦኦንይማ ከነገ ዓርብ ጀምሮ ከደቡብ አፍሪካ ወደ ናይጄሪያ መመለስ ለሚሹ ዜጎች በነፃ ዜጎችን የሚያመላልስ አውሮፕላን ደቡብ አፍሪካ  እንደሚላክና  ፈቃደኛ ለሆኑ ናይጄሪያውያን የነፃ የአየር ትራንስፖርት ግልጋሎት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡

ወደ ሀገራቸው የመመለስ ፍላጎቱ ያላቸው ዜጎች በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ የናይጀሪያ ከፍተኛ ኮሚሽን መረጃዎችን መውሰድ እንዳለባቸውም ተገልጿል፡፡

ከዚህ አስቀድሞ የናይጄሪያ ልዩ መልዕክተኛ ቡድን በዛሬው ዕለት በወቅታዊ የደቡብ አፍሪካ ሁኔታ ዙሪያ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ ጋር እንደሚወያይም ነው የሲጂቲኤን ዘገባ ያመለከተው፡፡

በደቡብ አፍሪካ በውጭ ሀገራት ዜጎች ላይ ያተኮረ ጥቃት መቀስቀሱን ተከትሎ በርካታ ሀገራት ዜጎቻቸው አስፈላጊውን የደህንነት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማስጠንቀቂያዎችን ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡