የአለም ባንክ ለኬንያ የ75 ቢሊዮን ሽልንግ ብድር ፈቀደ

የአለም ባንክ ኬንያ የጠየቀችውን የ75 ቢሊዮን ሽልንግ ብድር ፈቀዷል፡፡

ባለፈው የፈረንጆቹ መጋቢት ወር ኬኒያ ለአለም ባንክ በጻፈችው ደብዳቤ በጀቷን ለመደጎም አስቸኳይ ብድር እንዲሰጣት በጠየቀችው መሰረት ነው ይህ ብድር የተፈቀደላት፡፡

ገንዘቡ በኬንያ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል ሲሆን በተለይም የአርሶ አደሮችን ምርታማነት እና ገቢ ለማሳደግ ስራ እንደሚውል አበዳሪው ተቋም ገልጿል፡፡

በተጨማሪም በግብርናው ዘርፍ የሚስተዋለውን ስር የሰደደ ሙስና ለመዋጋትም ይውላልም ነው የተባለው፡፡

እንደ የአለም ባንክ ገለጻ ከሆነ ገንዘቡ በሃገሪቱ ግልጽ የሆነ የግብይት ስርዓት እንዲፈጠር እንዲሁም የመንግስት መስሪያ ቤቶች የግዢ ሂደትን ለማሻሻል ይውላል፡፡

ከዚህም ባሻገር ይህ ብድር በኬንያ ያለውን የኢንተርኔት አጠቃቀም ለማሳደግና የኢንተርኔት አገልግሎትን ለመላው ኬንያዊያን ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል፡፡/ሲጂቲኤን/