ኤጀንሲው በትግራይ ክልል በነበረው ህግ የማስከበር እርምጃ የምግብ ግብዓት እጥረት እንዳይከሰት እየተሰራ መሆኑ ገለጸ

የፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ 345 ሺህ ብር ድጋፍ አደረገ

የፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ የህወሓት ጁንታ ቡድን በሀገሪቱ የፈጠረውን የኢኮኖሚ እና የምግብ ግብዓት አቅርቦት ችግር ለመፍታት እና በትግራይ ክልል በነበረው ህግ የማስከበር እርምጃ በህብረተሰቡ ዘንድ የምግብ ግብዓት እጥረት እንዳይከሰት ቅድመ ዝግጅች እየተደረገ መሆኑን ገለጸ፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር ከዋልታ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት ከአዲሱ የትግራይ ክልል አመራር ጋር በመቀናጀት እና በመነጋገር በክልሉ የሚያጋጥሙ የምግብ ግበዓት አቅርቦቶችን ለመፍታት እና ለህብረተሰቡ የማቅረብ ስራ ይሰራል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ሁሉም በአንድነት መስራት አለበት ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ሁሉም ህብረተሰብ ከመንግስት ጎን በመሆን አጋርነቱን ማሳየት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

ያለፉት ጊዜያት በተለይም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እና የምግብ ግበዓት አቅርቦትን በብርቱ የፈተኑትን ኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የአንበጣ መንጋ እና ጎርፍ መሆናቸውን ገልጸው፣ የተፈጠሩ ችግሮችን በመለየት በርካታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውንም ተናግረዋል፡፡

ኤጀንሲው ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የ345 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በአስቸጋሪ መንገድ ሄደው ህዝባቸውን እና ሀገራቸውን ለማዳን ያደረጉትን ጥረት እንደሚያደንቁ የተናገሩት አቶ ኡስማን፣ ሀገር እና ህዝብን መውደድ በተግባር መገለጽ የሚችል መሆኑን በተግባር አሳይተዋል ብለዋል፡፡

(በሜሮን መስፍን)