በአዲስ አበባ 2‚300 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች መገንባታቸው ተገለጸ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ባሉት ትምህርት ቤቶች 2 ሺህ 300 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችና 118 የተማሪዎች መመገቢያ አዳራሾች መገንባታቸውን ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የመካኒሳ አካባቢ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የትምህርት ማስጀመሪያ መርኃግብር የተገኙት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ ሀገር ውስጥ ከገባ ጀምሮ ለጥቂት ወራት የመከላከያ ቁሳቁስና የግንዛቤ እጥረት ስለነበር ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ መደረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡
ይህም ትክክለኛ ውሳኔ እንደነበር አንስተው፣ አሁን ላይ ሁሉም ሰው በመከላከያ መንገድ ዙሪያ ግንዛቤ በመኖሩና መንግስትም የመከላከያ ቁሳቁስ ማምረት በመጀመሩ የመማር ማስተማር ስራ እንዲቀጥል መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በዚህም አጠቃላይ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲሳለጥና ተማሪዎች በትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ከተማ አስተዳደሩ ከምገባ ጀምሮ ሙሉ የትምህርት ቁሳቁስ አሟልቶላቸዋል ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የትምህርት ሂደቱ በፈረቃ ስለሆነ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች እና ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲመገቡ ተጨማሪ የመመገቢያ አዳራሾች መገንባታቸውን ምክትል ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ በከተማዋ ከ1 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ለተማሪዎቹ አስፈላጊ ጥንቃቄ ተደርጎ ትምህርቱ በሶስት ምዕራፍ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
አስተያየታቸውን ለዋልታ የሰጡት የትምህርት ቤቱ መምህራንና ወላጆች ከተማ አስተዳደሩ ለተማሪዎች ያደረገው የተለያዩ ድጋፎች ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
ለዋልታ አስተያየት የሰጡት ተማሪዎች በበኩላቸው፣ ከ7 ወራት በላይ ያለትምህርት በቤት መቀመጥ አሰልቺ መሆኑን ገልጸው፣ ቤተሰቦቻቸውን እያገዙና በጥናት ጊዜያቸውን ማሳለፋቸውን ተናግረዋል፡፡

አሁን ትምህርት ቤት በመከፈቱና ትምህርት በመጀመራቸው ደስተኛ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

(በአካሉ ጴጥሮስ)