የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የግል ጠበቃና የቀድሞው የኒውዮርክ ከተማ ከንቲባ ሩዲ ጁሊያኒ በኮቪድ-19 ከተያዙ በኋላ ወደ ሆስፒታል መግባታቸው ተገለጸ።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ የጠበቃቸውን ሆስፒታል መግባት በማስመልከት ጠበቃው ቶሎ እንዲሻላቸው ምኞታቸውን በትዊተር ገጻቸው ላይ ገልጸዋል።
ጠበቃው ጁሊያኒ ከምርጫው በኋላ የትራምፕን የፍርድ ቤት ክርክር ሲመሩ የቆዩ ናቸው።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን የ76 ዓመቱ ጠበቃ ሕመም ጸንቶባቸው ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ሜድስታር ጆርጅታዎን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል እንዲገቡ መደረጉን በስፋት ዘግበዋል።
የቀድሞ የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ የአሁኑ የፕሬዝዳንቱ ጠበቃ መልካም ምኞት የገለጹላቸውን አመስግነው ከሕመማቸው እያገገሙ እንደሆነ ገልጸዋል።
በዋይት ሐውስ የሚሰራው የጠበቃው ልጅ አንድረው ጁሊያኒ ወላጅ አባቱ እረፍት እያደረጉ እና እየተሻላቸው መሆኑን ገልጿል። ጠበቃው ጁሊያኒ የትኞቹን የበሽታው ምልክቶች እያሳዩ እንደሆነ አልተገለጸም።
እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ አሃዝ ከሆነ በአሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 14.6 ሚሊየን የተቃረበ ሲሆን፣ ከ281 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ሕመሞች ሕይወታቸው አልፏል። ይህም በዓለማችን ከፍተኛው ነው።
(ምንጭ፡-ቢቢሲ)