የጋና ፕሬዚዳንት ናና አኩፎ ለ2ኛ ጊዜ ምርጫ አሸነፉ

                                                የጋና ፕሬዚዳንት ናና አኩፎ አዶ

የጋና ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ በድጋሚ ምርጫ በማሸነፋቸው ተጨማሪ የአራት ዓመት የስልጣን ጊዜ እንዳገኙ የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

የ 76 ዓመቱ አኩፎ አዶ 51 ነጥብ 6 በመቶ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸውን የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ሃላፊ ጄን ሜንሳ ገልጸዋል።

ተቀናቃኛቸው ናሽናል ዴሞክራቲክ ኮንግረስ መሪ ጆን ማሃማ 47 ነጥብ 4 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውንም የኮሚሽኑ ሃላፊ አስታውቀዋል።

በ 38 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች 17 ሚሊየን መራጮች መሳተፋቸው የተገለጸ ሲሆን ፣ መራጮች ለብሔራዊ ፓርላማ 275 የሕግ አርቃቂዎች መምረጣቸውም ሲጂቲኤን አስነብቧል፡፡

አፍሪካ ህብረት፣ ኢኮዋስ እና የምዕራብ አፍሪካ የተባበሩት መንግስታት ጽህፈት ቤት በጋራ በሰጡት መግለጫ የጋና ህዝብ ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ በማከናወኑ አመስግነዋል።