ጆ ባይደን በመራጭ ወኪሎች የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው በይፋ ተሰየሙ

ጆ ባይደን የምርጫ ድላቸው በመራጭ ወኪሎች ስብስብ (ኤሌክቶራል ኮሌጅ) ተረጋግጦላቸው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው በይፋ ተሰይመዋል፡፡

ይህንን የድምጽ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ተከትሎ ባይደን ባደረጉት ንግግር “በመጨረሻም የሕዝቡ ፍላጎት አሸነፈ” ብለዋል።

በአሜሪካ የምርጫ አሰራር መሰረት ሕዝብ ድምጽ የሚሰጠው በቀጥታ ለእጩ ፕሬዝዳንቶች ሳይሆን የግዛት ወኪሎችን ለመምረጥ ነው፡፡ በዚህ መንገድ 270 እና ከዚያ በላይ ድምጽ ውክልና ያገኘ አሸናፊ ይሆናል፡፡

በመጨረሻ እነዚህ የድምጽ ሰጪ የግዛት ወኪሎች ተሰባስበው በሕዝብ የተቀበሉትን ውክልና በድምጻቸው በማረጋገጥ ፕሬዝዳንቱን በይፋ ይመርጣሉ፡፡

ባይደን በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸው በዚህ መንገድ በይፋ መረጋገጡን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር የአሜሪካ ዴሞክራሲ “ተገፍቶ፣ ተፈትኖ እና ስጋት ላይ ወድቆ ነበር” ካሉ በኋላ፤ የአሜሪካ ዴሞክራሲ፤ “እውነተኛ እና ጠንካራ መሆኑን አፈር ልሶ በመነሳት አረጋግጧል” ብለዋል።

ባይደን ፕሬዝዳንት ትራምፕ የምርጫውን ውጤት ለማስቀየር ያደረጉትን ጥረት ፍሬ ባለማፍራቱ አሁን ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ የምንሸጋገርበት ጊዜ ነው ብለዋል።

ይህ በኤሌክቶራል ኮሌጁ የሚሰጠው ማረጋገጫ ባይደን ወደ ዋይት ሃውስ እንዲገቡ ማግኘት የሚገባቸው የመጨረሻው ማረጋገጫ የድምጽ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ነው።

በአሜሪካ ምርጫ ስርዓት ውስጥ መራጮች ድምጻቸውን ለኤክቶራል ኮሌጅ መራጮች በየግዛቶቻቸው ከሰጡ በኋላ አሸናፊዎቹ “ኤሌክተርስ” በዚህ መንገድ ተሰባስበው ለፕሬዝዳንታዊ እጩዎች ድምጻቸውን ይሰጣሉ።

በአሜሪካ የምርጫ ውጤት መሠረት ዲሞክራቱ ጆ ባይደን ከወር በፊት በተካሄደው ምርጫ 306 ኤሌክቶራል ኮሌጅ ድምጽ ሲያገኙ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ደግሞ 232 ድምጽ ማግኘታቸው የሚታወስ ነው፡፡

እስካሁን የምርጫውን ውጤት አልቀበልም የሚሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ ባይደን ምርጫውን ማሸነፋቸው በአሌክቶራል ኮሌጅ ከተረጋገጠ በኋላ ያሉት ነገር የለም ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡