የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በጦር ኃይሎች ሪፈራል ሆስፒታል በመገኘት በህግ ማስከበር ዘመቻው የተካፈሉ የመከላከያ አባላትን ጎበኙ

የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ከመከላከያ ድጋፍ አሰባሳቢ የሚኒስትሮች አብይ ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን በጦር ኃይሎች ሪፈራል ሆስፒታል በመገኘት በህግ ማስከበር ዘመቻው ላይ የተካፈሉ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን ጎብኝተዋል።

ሚኒስትሯ በጉብኝቱ ወቅት “እኛ እዚህ የተገኘነው በአጥንታቸውና በደማቸው ስለ ሀገራቸውና ህዝባቸው ዋጋ የከፈሉ ወገኖቻችንን ባይመጥንም አክብሮታችንን እና አብሮነታችን ለመግለጽ ነው” ብለዋል።

የህግ የማስከበር ዘመቻው ብዙ ትምህርት የወሰድንበት ነው ያሉት ወ/ሮ ሙፈሪሃት፣ ዘመቻው ሀገርን የመውደድ ሚስጥር ምን ያህል እንደሆነ የታየበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለዘላቂ ሰላም የህግ የበላይነትን ማስከበር ዋነኛ ተግባር እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሯ፣ ከዚህ በኋላ በአብሮነት የተሰጠንን ኃላፊነት እንድንወጣ ሁኔታዎችን ያመቻቸና መስመር ያስያዘ ሂደት ነው ብለዋል።

በመጨረሻም በህግ ማስከበር ዘመቻ ላይ የተሳተፉትን የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የአማራና የአፋር ልዩ ኃይል ጨምሮ በሂደቱ የተሳተፉትን ሁሉ በመከላከያ ድጋፍ አሰባሳቢ የሚኒስትሮች አብይ ኮሚቴ ስም ሚኒስትሯ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በጉብኝቱ የመከላከያ ድጋፍ አሰባሳቢ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ሰብሳቢ የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚልን ጨምሮ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ የትራንስፖርት ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ እንዲሁም የሰራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉ መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።