በማዕድን ማምረት እና ምርምር ላይ የተሰማሩ 63 ተቋማት የስራ ፈቃድ ተሰረዘ

በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በማዕድን ማምረት እና ምርምር ሥራ ላይ እንዲሰማሩ ፈቃድ ከተሰጣቸው 213 ተቋማት ውስጥ 63 የሚሆኑት ባሳዩት አፈፃፀም ድክመት እና የህዝብና የመንግስት ሀብትን በማባከን የተሰጣቸው ፈቃድ ተሰርዟል።

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስት ኢ/ር ታከለ ኡማ ፈቃዳቸው በተሰረዘው ተቋማትና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ሚኒስትሩ እንደገለጹት ፈቃዳቸው ከተሰረዘባቸው 63 ተቋማት ውስጥ 38 ተቋማት በማዕድን ምርት ላይ የተሰማሩ ሲሆን፣ 25ቱ ደግሞ በማዕድን ምርምር ላይ ተሰማርተው የነበሩ ናቸው።

ተቋማቱን ወደ መስመር ለማስገባት ብዙ ጥረት እንደተደረገ የተናገሩት ኢንጅነር ታከለ የተቋማት ፈቃድ የተሰረዘው በአዋጁ በተሰጠው መስፈርቶች መሆኑን ጠቁመዋል።

ፈቃዳቸው የተነጠቀባቸው የማዕድን ቦታዎች በአፋጣኝ ወደ ስራ እንዲገቡና የማዕድን ሀብቶችን በተገቢው መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚደረግ መሆኑም ተገልጿል።

በሌላ በኩል 4 ሺህ 83.2 ኪ.ግ ወርቅ ለውጭ ገበያ ቀርቦ 299.1 ሚሊየን ዶላር ከውጭ ምንዛሪ፣ ከጌጣ ጌጥ ማዕድናት ደግሞ 3.8 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ባለፉት አምስት ወራት ከማዕድን ዘርፍ 302.9 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱንም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

ይህም ከማዕድን ዘርፍ የሚገኘው ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚገኝ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የተገኘው ገቢ የኮንትሮባንድ ንግድን ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር በተሠራው የቅንጅት ስራ የተገኘ ውጤት በመሆኑ በቀጣይም ከዘርፉ የሚፈለገውን ያህል ጥቅም ለማግኘት የቅንጅት ስራው ሊቀጥል እንዲሁም የማዕድን ምርት ማነቆ የሆኑ የመሠረተ ልማት እና የአቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ሚኒስቴሩ ከክልሎች ጋር በመናበብ ይሠራል ነው ያሉት ሚኒስትሩ በመግለጫቸው፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የማዕድን ሀብት ወደ ግዙፍ የኢንቨስትመንት ደረጃ ማደግ የሚችል በመሆኑ ለዚህም የሀገርና የህዝብ ሀብት የሆነውን ማዕድን በተገቢው ጊዜ እና መልክ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

(በድልአብ  ለማ)