መንግስት ወደ ሱዳን የተሰደዱ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር ለመመለስ እየሰራ ነው- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

መንግስት ወደ ሱዳን የተሰደዱ ኢትዮጵያውያንን ከሱዳን መንግስት ጋር በመነጋገር ወደ ሀገር ለመመለስ እየሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ፣ በትግራይ ክልል በነበረው አለመረጋገት እስካሁን 40 ሺህ ተፈናቃዮች ወደ ሱዳን መሰደዳቸውን ገልጸው፣ ወደ ሀገር ለመመለስ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ከስደተኞቹ መካከል በወንጀል የተሳተፉና የሸሹ ስለሚኖሩ መንግስት በትኩረት እየሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

የቀይ መስቀልና ሌሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ለስደተኞች ድጋፍ ማድረግ የሚችሉበት ሁኔታ እንደተመቻቸም አምባሳደር ዲና  ጠቁመዋል፡፡

በትግራይ ክልል የተለመደ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ተጀምሯል ያሉት ቃልአቀባዩ፣ በክልሉ የስልክ፣ የመብራትና ሌሎች መሰረተ ልማቶች መስተካከላቸውንና ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የሚደረጉ በረራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) መቀሌ ሄደው ከሰራዊቱ አባላት ጋር መወያየታቸው በክልሉ ሰላም መምጣቱን ማሳያ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በወቅታዊ የትግራይ ክልል ሁኔታ ላይ ገለጻ ማድረጋቸውንም በመግለጫቸው አመልክተዋል፡፡

(በመስከረም ቸርነት)