የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር አብርሃም በላይ በአዲግራት ከተማ ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዩች ዙሪያ ውይይት አደረጉ።
በውይይቱም የሀገር ሽማግሌዎቹ ተቋርጦ የቆየው በተለይም የመብራት፣ ቴሌኮምና የውሃ አቅርቦት በአፋጣኝ ወደ አገለገሎት እንዲመለስላቸው ጠይቀዋል።
ዶክተር አብርሃምበጁንታው የወደሙ መሰረተ ልማቶች በአፋጣኝ ወደ አገልግሎት እንዲመለሱ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም የመቀሌ ውቅሮ እና አዲግራት የኤሌክትሪክ መስመር ጥገና ተጠናቆ በሁለት ቀናት ውስጥ የመብራት አገልግሎት ይጀምራል ብለዋል።
የሃገር ሽማግሌዎቹም የህወሃት ቡድን የህዝብ መሰረተ ልማቶችን በማውደም ነዋሪውን ለችግር በመዳረጉ ማዘናቸውን ገልጸዋል።
በተለይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የውሃ አቅርቦትና የህክምና ተቋማት ላይ ባደረሰው ጥፋት ህዝቡ ችግር ላይ መቆየቱን ተናግረዋል።
ዶክተር አብርሃም በሰጡት ማብራሪያም ጁንታው ለህዝቡ ደንታ የሌለውና የህዝብ ጠላት በመሆኑ የህዝብ መገልገያ የመሰረተ ልማቶችን አውድሟል ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜም የወደሙ የመሰረተ ልማቶችን በከፍተኛ ርብርብ በመጠገን አገልገሎት እንዲጀምሩ እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በአዲግራትና ውቅሮ ከተሞችም ተቋርጦ የነበረው የመብራት አገልግሎት በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ዳግም ይጀመራል ብለዋል።
በጁንታው የወደሙ ሌሎች መሰረተ ልማቶችንም መልሶ የመገንባት ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህ ሂደት ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመሆን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ዶክተሩ አብርሃም ጥሪ አቅርበዋል።
በአዲግራት ከተማ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን ኢዜአ ዘግቧል።