የንግድ ትራንስፖርት አደረጃጀት ብቃት ማረጋገጫና አፈፃፀም መመሪያን በተመለከተ ውይይት ተካሄደ

የኢፌዴሪ የትራንስፖርት ሚኒስቴር የንግድ የትራንስፖርት አደረጃጀት ብቃት ማረጋገጫ እና አፈፃፀም ላይ ባወጣው መመሪያ ዙሪያ የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ማህበር አባላት በተገኙበት ውይይት አካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኔ ዘርኡ የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመንና በሚፈለገው ልክ ለመምራት የሚያስችሉ መመሪያዎችና አዋጆችን ማውጣት የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሃላፊነት ሲሆን፤ አዋጆች በሚወጡበት ወቅት የሀገሪቱን እድገት የሚያፋጥን እንዲሁም በትራንሰፖርት ዘርፉ ላይ የተሰማሩ አካላትንም የሚደግፍ እና የሚያጠናክር መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ሆኖም በትራንስፖርት ሚኒስቴር የወጣው ይህ መመሪያ የጋራ ተጠቃሚነትን ብሎም የሀገርን እድገት የማያፋጥን በመሆኑ መመሪያውን ማሻሻል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን የቀረበውን ጥያቄ ምላሽ መስጠት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጠናክር በመሆኑ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ችላ ሊለው የሚገባ ጉዳይ አይደለም ሲሉም የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ ሀገራት የጭነት ማመላለሻ ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ እጅጉ መመሪያው በሀገራዊ የሎጅስቲክ አደረጃጀት እስካሁንም ያልተሻገርነው ነባራዊ ችግር ሆኖ ስለመቀጠሉ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ለበርካታ ማህበራት መፍረስ ምክንያት የሆነውን ይህን መመሪያ ማሻሻያ እንዲደረግለት ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ያቀረብን ቢሆንም፤ ተጨባጭ የሆነ መፍትሔ ማግኘት እንዳልተቻለና በዚህም መሰረት ቀጣይ እርምጃችን ሊሆን የሚችለው ጉዳዩን ወደ ህግ አካል የማቅረብ ነው ብለዋል፡፡

ፌዴሬሽኑም መመሪያው ተፈፃሚ እንዳይሆን የማህበሩ አባላት ፊርማን በማሰባሰብ ጉዳዩ እልባት ያገኝ ዘንድ ወደ ህግ የማቅረብ ስራ እየሰራ ይገኛልም ተብሏል፡፡

(በሄብሮን ዋልታው)