በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር አካባቢ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከተሳሳተ ግምት የመነጨ ነው – አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር አካባቢ የተስተዋለው የፀጥታ ችግር በተወሰኑ የሱዳን ሚሊሻዎች እና ጥቂት ወታደሮች የተሳሳተ ግምት በመነጨ በድንበር አካባቢ ተኩስ በመክፈታቸው ምክንያት የተፈጠረ እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።

አምባሳደር ዲና በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የህወሓት ጁንታ በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መንግሥት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ህግ የማስከበር ሥራ ላይ ባለበት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጰያ በድንበር አካባቢ ትኩረት አይሰጥም በሚል የተሳሳተ ግምት የተወሰኑ የሱዳን ሚሊሻዎች እና ጥቂት ወታደሮች የተሳሳተ ግምት በመነጨ በድንበር አካባቢ ተኩስ ከፍተዋል።

ይሁን እንጂ መንግሥት ሙሉ ትኩረቱን በሰሜን የህግ ማስከበር ላይ ቢያደርግም በድንበር አካባቢም የጸጥታ ችግር እንዳይከሰት በትኩረት እየሠራ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ዲና፤ በድንበር አካባቢ ያሉ የሱዳን ሀይሎች ግን “የኢትዮጵያ መንግሥት በድንበር አካባቢ ትኩረት አይስጥም” በማለት በተሳሳተ ግምት የድንበር አካባቢ ህዝባችን ለማጥቃት ተኩስ የከፈቱ ቢሆንም በመከላከያ ሠራዊትና በአካባቢው ሚሊሻ እንደ ተመከቱ ተናግረዋል። የደረሰ ጉዳት ካለም የጉዳቱ መጠን ለወደፊት ተጣርቶ የሚገለጽ ይሆናል ብለዋል።

እንደ አምባሳደር ዲና ገለጻ፤ ግጭቱ የሁለቱም አገራትም መሪዎችም ፍላጎት አይደለም። የኢትዮጵያ መንግሥትም ጉዳዩን አስመልክቶ ከሱዳን ጋር ተነጋግሯል። በቀጣይም በአካባቢው አልፎ አልፎ ለሚከሰተው ችግር መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘላቂ እልባት እንዲያገኝ ይሰራል። የተጀመረው የህግ ማስከበር ስራም በአጭር ጊዜ ውስጥ ስለተጠናቀቀ ወንጀለኞችንም አድኖ ለመያዝ ከሱዳን መንግሥት ጋር በቅርበት እየሰራ ይገኛል።

በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖርና አርሶ አደሩ ምርቱን በአግባቡ እንዳይሰበስብ ፍላጎታቸውን በትርምስ ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች በርካታ መሆናቸውን የገለጹት አምባሳደር ዲና፤ ኢትዮጵያ ግን የሁለቱም አገራት ዘላቂ ጥቅሞች በሚያስከብር መልኩ ከሰዳን ጋር እንደምትሰራ፣ እየሰራችም እንደ ሆነ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ ሰሞኑን ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት “የተፈጠረውን ችግር ለማባባስ የሚጥሩ ኃይሎች፣ የኢትዮጵያና የሱዳን ታሪካዊ ትስስር ካለማወቅና ችግሮቻቸውን በድርድር ሲፈቱ መቆየታቸው ካለመገንዘባቸው የተነሳ ነው” ማለታቸው አይዘነጋም።