የበረሃ አንበጣ መንጋ ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ እየገባ መሆኑ ተገለጸ

የአንበጣ መከላከል ተግባር

የግብርና ሚኒስቴር በሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ባካሄደው የመስክ ምልከታ አዲስ የተራባው የበረሃ አንበጣ መንጋ ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ እየገባ መሆኑን ገልጿል፡፡

ወቅታዊ የአየር ሁኔታ ለመራባት ምቹ በመሆኑ በምስራቅ ኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ሰፊ እርባታ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል ነው የተባለው፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ በላይ ንጉሴ በመራባት ላይ የሚገኝ የበረሃ አምበጣ መንጋ ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ እየገባ መሆኑን ከስፍራው ለዋልታ ተናግረዋል፡፡

በሶማሌ ክልል፣ በምስራቅ ኦሮሚያ እና በደቡብ ክልል ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ በ13 አውሮፕላኖች የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት አቶ በላይ፣ በመኸር ሰብል ላይ ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

ፋኦ ለኬሚካል ርጭት የሚያገለግሉ አውሮፕላኖች፣ መኪኖች፣ ኬሚካሎች እንዲሁም የገንዘብ እና  የባለሙያ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ የአንበጣ መንጋ መከላከል የሚቻለው አገራት በትብብር መስራት ሲችሉ በመሆኑ በምስራቅ አፍሪካ የአንበጣ መከላከል ድርጅት ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ከ35 ሚሊየን በላይ ሰዎች ከፍተኛ የምግብ እጥረት ባለባቸው ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን እና መንጋውን መቆጣጠር ካልተቻለ ተጨማሪ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች ለከፍተኛ የምግብ እጥረት እንደምዳረጉ የፋኦ መረጃ ያመለክታል፡፡

በሚቀጥሉት ወራት መንጋው ለኤርትራ፣ ለሳውዲ አረቢያ፣ ለሱዳን እና ለየመን አዲስ ስጋት እንደሚሆንም ተጠቁሟል፡፡

 

(በትዝታ መንግስቱ)