በትግራይ ክልል በርካታ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ዘመቻ ላይ የሚገኙ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ባከናወኗቸው የፍተሻ ስራዎች ጁንታው አገር ማፍረስ ተልዕኮው ይገለገልባቸው የነበሩ በርካታ የጦር መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸው ተገለፀ፡፡

በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ የክትትል ኦፕሬሽንና አስገዳጅ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮማንደር ጥላሁን ወልደ ትንሳኤ በትግራይ ክልል ሀገራዊ ግዳጅ ላይ የተሰማሩ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ከፍተሻ ስራ በተጓዳኝ ማህበረሰቡን የማረጋጋት ስራዎችን ማከናወናቸውን ተናግረው ሰራዊቱ ባደረገው ጥረት በክልሉ የበለጠ መረጋጋት መፈጠሩን ጠቁመዋል፡፡

በትግራይ ክልል በመከናወን ላይ የሚገኘው ህግን የማስከበር የህልውና ዘመቻ ውጤታማ መሆኑን የገለፁት ኮማንደር ጥላሁን በተለያዩ ስፍራዎች ለእኩይ አላማ እንዲውሉ የተዘጋጁና ከሰራዊቱ እይታ የተደበቁ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ዘመናዊና ኋላ ቀር መሳሪያዎች ለታለመላቸው ድርጊት እንዳይውሉ የማምከን ስራዎች ማከናወናቸውን ገልፀዋል፡፡

በፌደራል ፖሊስ የኮማንዶ ዲቪዥን ሻለቃ አዛዥ ምክትል ኮማንደር መሃመድ አሰፋ በበኩላቸው በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና ማህበረሰቡ ያለ ፀጥታ ስጋት መንቀሳቀስ እንዲችል ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከሀገር መከላከያ ሰራዊትና ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራርን በመፍጠር በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ጁንታው ለፀረ-ሰላም ተግባር የሚጠቀምባቸው በግልና በቡድን የሚያዙ የጦር መሳሪያዎችና ጥይቶች በሰራዊቱ እየተያዙ መሆናቸውን የገለፁት በመቀሌ ከተማ የህግ ማስከበር ስራ ላይ የሚገኙ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አመራርና አባላት እነዚህን የጦር መሳሪያዎች ለመቆጣጠር በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ህብረተሰቡ የጎላ ሚና እንዳለው ተጠቁሟል፡፡