ከተማ አስተዳደሩ የ10 አመታት የትራንስፖርት ስትራቴጂ ላይ ውይይት እያካሄደ ነው

 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ10 አመታት የትራንስፖርት ስትራቴጂ ላይ ውይይት እያካሄደ ነው።

ስትራቴጂው የአዲስ አበባ ከተማን ሁሉ አቀፍ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ለመምራት እና የትራንስፖርት ልማት ለማሳለጥ የሚያገለግል ፍኖተ ካርታ እንደሆነ ተገልጿል።

የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ስጦታው አካለ ስትራቴጂው በቀጣዩ 10 አመታት የከተማዋን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማዘመን ሰፊ ሚና እንደሚኖረው እና ዘመናዊ የትራንስፖርት ስርዓትን እውን ለማድረግ እንደሚረዳ ተናግረዋል።

የስትራቴጂው ዋነኛ አላማ በከተማዋ ቀልጣፋ፣ ሉሁሉም ተደራሽ፣ ደህንነቱ የተረጋገጠ እና ዘላቂ የትራንስፖርት ስርዓት እንዲኖር ለማስቻል እንደሆነ ጠቁመዋል።

ስትራቴጂው ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በመስራት ላይ እንደነበር የተገለፀ ሲሆን፣ በየደረጃው ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ መቀረጹንም ተናግረዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ስትራቴጂውን በማዘጋጀት ሰፊ ድርሻ የነበራቸውን የተቋሙን አካላት እና ሌሎች ተሳታፊዎችን አመስግነዋል።

የከተማዋ የትራንስፖርት ስትራቴጂ ጽሁፍ በመድረኩ የቀረበ ሲሆን፣ በትራንስፖርቱ በኩል ከተማዋ እያጋጠማት ያሉ ችግሮች ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

(በሄለን ታደሰ)