በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃ የእስራኤል ባለሀብቶችን ቀልብ ስቧል- አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃ የእስራኤል ባለሀብቶችን ቀልብ መሳቡን በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ ገለጹ።

እስራኤል በኢትዮጵያ ለተጀመረው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራ ድጋፍ እንደምታደርግም አመልክተዋል።

በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲና የእስራኤል አፍሪካ የንግድ ምክር ቤት በመተባበር በኢንቨስትመንት ጉዳይ ላይ ያዘጋጁት የበይነ መረብ የውይይት መድረክ ትናንት ተካሄዷል።

በውይይቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ጽዮን ተክሉ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁንና በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ ተሳትፈዋል።

በእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካና ላቲን አሜሪካ ኢኮኖሚ ጉዳዮች ዳይሬክተር ሚስ ሚሃል ጉር-አርዬህ፣ የእስራኤል ባለሃብቶች የንግድ ማህበረሰብ አባላት እንዲሁም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች ተወካዮች መሳተፋቸው ነው የተገለጸው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ጽዮን ተክሉ መንግስት ነጻነትን እና ብልጽግናን በኢትዮጵያ ለማስፈን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

“ከማሻሻያ እርምጃዎች ውስጥ በግሉ ዘርፍ የሚመራ ሁሉን አቀፍና ዘላቂ ልማት መፍጠር አንዱ ነው” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡