የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ እንደሚገነዘብ አስታወቀ

 

በጄኔቭ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ቋሚ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዘነበ ከበደ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጠና ዋና ኃላፊ ለሆኑት ፍራንኳይስ ሚያንዳ መንግስት በትግራይ ክልል ስለወሰደው የሕግ ማስከለበር ዘመቻ ገለፃ ሰጥተዋል።

የሕወሀት ጁንታ የተደራጀ ምዝበራ እና በወታደራዊ ኃይል የታገዝ መጠነ ሰፊ የሕግ ጥሰት ሲፈፅም መቆየቱንና የአገሪቷን ሕልውና ጭምር አደጋ ላይ ለመጣል ሌት ተቀን ሲሰራ መቆየቱን ገልፀውላቸዋል።

በአገሪቱ እየተተገበረ ባለው መሠረታዊ የለውጥ ሥራ ዘርፈ ብዙ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ መሻሻሎች እየተመዘገቡ ቢሆንም፣ ይኼው ቡድን የለውጡ አካል ሆኖ በሠላማዊ መንገድ ከመንቀሳቀስ ይልቅ፣ ለውጡን ቀልብሶ ወደ ስልጣን በመመለስ የፖለቲካ ተጽዕኖውን እና የኢኮኖሚ ምዝበራውን ለማስቀጠል አገርን የማተራመስና ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ ላይ ተሰማርቶ መቆየቱን ገልጸዋል።

መንግስት ያሳየውን ሆደ ሰፊነት እንደ ድክመት እና ፍርሀት በመውሰድ የመከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝን በማጥቃት እና ከባድ መሳሪዎችን በመዝረፍ ፈጽሞ ከስህተቱ የማይማር ድርጅት መሆኑን እንደሚያሳይም አብራርተዋል።

በዚህ ተግባሩ ቀይ መስመር ያለፈ በመሆኑ፣ መንግስት የተጣለበትን ሕገ መንግስታዊ ስርዓት የማስከበር እና የአገሪቱን አንድነት ለማስጠበቅ ወደ እርምጃ ለመግባት መገደዱን አከወለው ገልፀዋል።

በትግራይ ክልል የተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ዓላማ በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በማድረስ ከባድ የአገር ክህደት ወንጀል የፈፀመውን የሕወሀት ጁንታ ይዞ ለሕግ ለማቅረብ፣ ያሰማራቸውን የጥፋት ኃይሎች ትጥቅ በማስፈታት በክልሉ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ማድረግ መሆኑን ገለፃ ሰጥተዋል።

በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት ጊዜያዊ አስተዳደር ተመስርቶ ሕዝቡን መልሶ ማቋቋምና አስፈላጊ የሰብዓዊ ድጋፍና እርዳታን ከሚመለከታቸው አገራዊ እና ዓለምአቀፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ የማቅረብ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ያወሱት አምባሳደሩ፤ የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሉዓላዊና ሕጋዊ የውስጥ ጉዳይ ስለመሆኑ አስምረውበታል።

በሕግ ማስከበር ዘመቻው ውስጥ መከላከያ ሰራዊት የሚወስዳቸው እርምጃዎች በተመረጡ ኢላማዎች ላይ ብቻ መሆኑን ገልጸው፤ በሠላማዊ ሠዎች ላይ ጥቃትና አደጋ እንዳይደርስ በከፍተኛ ጥንቃቄ የተከናወነ መሆኑን፣ የዜጎች የሰብዓዊ መብቶች እና ሰብዓዊ ጉዳዮች ቅድሚያ የተሰጠው በመሆኑን ገልጸዋል።

ይህም መንግስት ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ቁርጠኝነት እንዳለው የሚያሳይ መሆኑንም አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት ሕግ የማስከበር ዘመቻው መጠናቀቁን፣ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን እና ሕብረተሰቡ ወደ ዕለት ተዕለት ኑሮው እየተመለሰ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከዚህ በኋላ የሚቀረው የጁንታው ቡድን አባላትን አድኖ ወደ ሕግ ፊት የማቅረብ ስራ መሆኑን እና ይህም በፌዴራል ፖሊስ በኩል እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በተጨማሪም የስልክ፣ የመብራት እና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች በተሻለ ሁኔታ ተደራሽ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን እንዲሁም የተፈናቀሉ ዜጎችም ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ የመልሶ ማቋቋም ስራዎች እየተከናወኑ ስለመሆናቸው ገለፃ አድርገዋል።

መንግስት ከዓለምአቀፍ የሰብዓዊ ተቋማት ጋር ተባብሮ እየሠራ መሆኑንና ይኼው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀው፣ ወደ ጎረቤት አገር የሸሹ ዜጎቻችንም ወደ አገራቸው ተመልሰው የሚቋቋሙበት ሁኔታ ከሚመለከታቸው የውስጥና የውጭ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ፣ ለዚሁም አራት የመጠለያ ካምፖች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል።

በክልሉ ያለውን የሰብዓዊ ሁኔታ ለማጥናት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የጥናት ቡድኖችን ልኮ ካጣራ በኋላ የሰብዓዊ እርዳታ ኮሪዶር በመክፈት አስፈላጊውን ድጋፍ ማከፋፈል ላይ መሆኑን፣ በሠላም ሚኒስቴር አስተባባሪነትም ከዓለምአቀፍ ማህበረሰብ ጋር በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ ለማቅረብ እንዲቻል እርምጃዎች መወሰዳቸውን አስረድተዋል።

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጠና ዋና ኃላፊ ፍራንኳይስ ሚያንዳ በበኩላቸው ጽህፈት ቤቱ እንደሰብዓዊ መብቶች ተቋም የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች እንዳይጣሱ፣ ተፈናቃዮች ተገቢው የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸውና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ፣ ለዚህም መንግስት አስፈላጊውን ሁኔታ እንዲያመቻች ከማበረታታት ባሻገር በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌለው አመልክተዋል።

መንግስት እየወሰዳቸው የሚገኙ አዎንታዊ እንቅስቃሴዎችን በቅርበት እንደሚከታተልና እንደሚደግፍም ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።