የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማትን በዘላቂነት መምራት የሚያስችል መሪ ዕቅድ ይፋ ሆነ

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማትን በዘላቂነት መምራት የሚያስችል መሪ ዕቅድ ይፋ ሆነ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማትን በዘላቂነት መምራት የሚያስችል ስፓሻል መሪ ዕቅድ ይፋ ተደረገ።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሸን የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ዕድገት ለማሳካትና ለመምራት የሚያስችል ሀገራዊ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ስፓሻል ጥናት ረቂቅ ሪፓርት ላይ የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል።

በመድረኩ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በዚህ ወቅት ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ ለሚቀጥሉት 20 ዓመታት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ዘለቄታዊ ልማት የሚመራ ስፓሻል ጥናት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ጥናቱ እንደ አገር የመጀመሪያ መሆኑንና ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት የመሬት ሁኔታ በማየት የተዘጋጀ ነው ብለዋል።

አሁን ያሉትን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከመምራት ባለፈ ወደ ፊት የሚመሰረቱ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ከምስረታቸው ጀምሮ በማገዝና በመምራት ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ፣ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስና በየትኛው አካባቢ ምን አይነት ኢንደስትሪ ፓርክ መገንባት አለበት የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማትን በዘላቂነት ለመምራት ይፋ በሆነው ስፓሻል መሪ ዕቅድ ላይ የመድረኩ ተሳታፊዎች እየተወያዮበት ሲሆን በዕቅዱ ላይ መሻሻል ያለባቸውን ነገሮች እንደሚያነሱ ይጠበቃል።

(ምንጭ፡- ኢዜአ)