ሚኒስቴሩ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ማደራጃ አዋጅን ለማሻሻል እየመከረ ነው

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድና ዘርፍ ማህበራት ማደራጃ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት፣ ከሀገር አቀፍና ከክልል ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ፕሬዘዳንቶች እና ከከልል ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊዎችና ሌሎች ዘርፉ ከሚመለከታው ኃላፊዎች ጋር ረቂቅ አዋጁን ለማሻሻልና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ሀሳብ የተካተተበትና የተሻለ አዋጅ ሆኖ ይዘጋጅ ዘንድ በኢንተር ኮንቲነታል ሆቴል ውይይት እያካሄደ ነው፡፡

በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድ ማስፋፊያና ሪጉላቶሪ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እሸቴ አስፋው እንደገለፁት ሀገራችን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የምታደርገው ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር ግቡን ሊመታ የሚችለው በንግዱ ብሎም በአምራች ዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ሚናቸውን በአግባቡ ሲወጡ ነው፡፡

የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቱ ለረጅም አመታት ያገለገለ በመሆኑ አሁን ካለው ሁኔታ ጋር አብሮ የማይሄድ በመሆኑ የንግዱን ማህበረሰብ ብሎም አምራቾችን ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ጉድለቶች የሚታዩበት በመሆኑ ማሻሻል አስፈላጊ እንደሆነ አቶ እሸቴ አስፋው ገልፀዋል፡፡

ሚኒስቴር ዴኤታው አክለውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን በውድድር ላይ የተመሰረተ የንግድ ስርዓት ለማስፈን ብሎም የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በረቂቅ አዋጁ የምክክር መድረክ ላይ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ፕሬዘዳንት ኢንጅነር መላኩ እዘዘው በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ 18 አመታትን ያሥቆጠረ በመሆኑ የዘርፉን የአሰራር ማነቆዎች በሚያስወግድ መልኩ ይሻሻል ዘንድ የሚመለከታቸውን የዘርፉ ተዋናዮች ሀሳብ እንዲያካትት ለማረግ በተለያዩ ጊዜያት ውይይት እንደተደረገበት ጠቅሰው የሀገር አቀፍና ክልል ዘርፍ ማህበራት ፕሬዘዳንቶችና የክልል ንግድና ኢንዱስት ቢሮ ኃላፊዎችም ለረቂቅ አዋጁ ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦችን በማንሳት ለአዋጁ መሻሻል የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል፡፡(ምንጭ ፡- የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር)