የቦረናን እና የደቡብ ኦሞ ዞኖችን የሚያገናኘው መንገድ ከ2 ወር በኋላ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል

 

የቦረናን ዞን ከደቡብ ኦሞ ዞን የሚያገናኘው መንገድ ግንባታው ተጠናቆ ከሁለት ወር በኋላ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ተገለጸ፡፡

የመንገዱ መገንባት የሁለቱን ዞኖች ብሎም የኦሮሚያ እና ደቡብ ክልል ህዝቦች በምጣኔ ሀብት፣ በንግድ እና በማህበራዊ ጉዳዮች ያሏቸውን ትስስሮች ለማጠናከር ይረዳልም ተብሏል፡፡

በ2011 ዓ.ም የተጀመረው ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ከቦረና ዞን ተልተሌ ከተማ እስከ  ደቡብ ኦሞ ዞን ዋና ከተማ ጂንካ ድረስ የሚዘልቅ ሲሆን ለአካባቢው ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝም ይጠበቃል፡፡

በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በም/ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት አሰተባባሪ  ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የተመራው ልዑክ ፕሮጀክቱን የጎበኘ ሲሆን የተልተሌ ወረዳ በእርሻ የሚታወቅ አካባቢ መሆኑም ተመልክቷል።

ይሁን እንጂ ለዘመናት የመንገድ መሠረተ ልማት ባለመኖሩ የአካባቢው አርሶአደሮች ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ ለማቅረብ ረጅም መንገድ ለመጓዝ ይገደዱ እንደነበር ነው በጉብኝቱ ወቅት የተገለጸው።

የመንገድ ፕሮጀክቱ 80 ኪሎሜትር  ርዝመት ያለው ሲሆን ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ እየተገነባ ይገኛል።

ግንባታው በሁለት ሎት ተከፍሎ እየተከናወነ ሲሆን በተያዘለት ጊዜና የጥራት ደረጃ እየተከናወነ አፈጻጸሙም 96 በመቶ ላይ መድረሱም ተጠቁሟል።

የመንገዱን ወጭ የሚሸፍነው የኦሮሚያ ክልል መንግስት ሲሆን የመንገዱ 10 ኪሎሜትር በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ውስጥ የሚገኝ ነው።

መንገዱ የቱሪስት መዳረሻ የሆነውን የደቡብ ኦሞ ዞን ለሚጎበኙ ቱሪስቶች አማራጭ መንገድ በመሆን  እንደሚያገለግልም ተነግሮለታል፡፡

የመንገዱ መሰራት እንዳስደሰታቸው የጠቆሙት ዋልታ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች የዘመናት ጥያቄያቸው እንደተመለሰላቸው ገልፀዋል።

በሚልኪያስ አዱኛ