የሀገርና የህዝብን ክብር ጠብቆ ማስቀጠል የሚችል ወጣት መገንባት ይገባል- የአማራ ብልጽግና ፓርቲ

የሀገርና የህዝብን ክብር ጠብቆ ማስቀጠል የሚችል ወጣት መገንባት የሁሉም አጀንዳ ሊሆን ይገባል ሲል የአማራ ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ።

“በኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ግንባታ የወጣቶች ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ክልል አቀፍ የወጣቶች መድረክ በባህር ዳር ከተማ ዛሬ ተጀምሯል።

የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኅላፊ አቶ አብርሃም አለኸኝ በወቅቱ እንደገለጹት ለጠንከራ ሀገረ መንግስት ግንባታ በምክንያታዊነት የሚያምን ወጣት የማይተካ ሚና አለው።

“ወጣቱ የሚነገሩና የሚጻፉ ትርክቶችን ከሃገርና ህዝብ ጥቅም አንጻር በማመዛዘን ለውጥ ለማምጣት የሚሰራ መሆን አለበት” ብለዋል።

“ሀገሪቱ አሁን ላለችበት ምስቅልቅል ውስጥ እንድትገባ ያደረጋት የህዝብና የሃገር ፍቅር በጎደላቸው ሰዎች ስትመራ መቆየቷ ነው” ያሉት ኅላፊው፤ ሁኔታው ለዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና ንብረት ውድመት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

ወጣቱ ትውልድ ክቡር ለሆነው የሰው ህይወት ጥበቃና ከለላ የሚሰጥ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

የሀገርና የህዝብን ክብር ጠብቆ ማስቀጠል የሚችል ወጣት መገንባት የሁሉም አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባም ኅላፊው አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል ወጣቶች ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ወጣት ጋሻው ተቀባ  በበኩሉ “ወጣቱ ከአባቶቹ ታሪክ መልካም ተግባራትንና ስኬቱን ወስዶ አሁን የመጣውን ለውጥ ዳር ለማድረስ በጋራ መስራት አለበት” ብሏል።

የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና የሚረጋገጠው ባሉት የተፈጥሮ ሃብት ብቻ ሳይሆን የትውልድ አሻራን የሚያስቀጥል ወጣት መፍጠር ሲቻል መሆኑንም አመልክቷል።

“ወጣቱ ህወሃት የዘራውን የዘር ፖለቲካና የፈጠረውን የተሳሳተ ትርክት በማረምና ራሱን በምክንያታዊነት በማነጽ ሀገርን ለመገንባት የሚነሳሳበት ወቅት ላይ ነው” ብሏል።

ፌደሬሽኑም የወጣት አቅም በመገንባት በሃገራዊ ግንባታው የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ እየሰራ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አስታውቋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የፖሊሲ አማካሪ አቶ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ “ሀገረ መንግስት እሳቤና የወጣቶች ሚና” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፍ ኢትዮጵያ በሃገረ መንግስት ግንባታ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን አመልክተዋል።

“ይሁን እንጂ ሃገረ መንግስቱን አጽንቶ እንዳይዘልቅ ያደረገውን ስር የሰደደን ድህነትና ኋላ ቀርነት መቅረፍ አልተቻለም” ብለዋል።

የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ባለመቻሉና በየጊዜው የነበሩ መንግስታት በህዝቡ ዘንድ የነበራቸው ቅቡልነት አናሳ በመሆኑ አሁን የሚስተዋለው ዘርፈ ብዙ ችግር እንዲከሰት ማድረጉን ጠቁመዋል።

ቅቡልነትን ለማረጋገጥና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት ወጣቱ ነጻ፣ ገለልተኛና ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በመድረኩ ከክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የተውጣጡ ወጣቶች እየተሳተፉ  መሆኑን ኢዜአ አግቧል።