በሐረሪ ክልል ፈቃድ ሳይኖራቸውና ሲነግዱ የተገኙ 720 ሱቆች ታሸጉ

በሐረሪ ክልል ፈቃድ ሳይኖራቸውና ግብር ሳይከፈሉ ሲነግዱ የተገኙ 720 የንግድ ሱቆች መታሸጋቸውን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ገለጸ።

በክልል ግብር ሳይከፍሉ በህገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎችን ሥርዓት ለማስያዝ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል።

የቢሮው ሃላፊ ወይዘሮ ሠሚራ ዩስፍ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ እየተበራከተ የመጣው ህገ ወጥ እና ያለፈቃድ የሚካሄድ የንግድ ሥራ በህጋዊ ነጋዴው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው።

ይህንን ችግር ለማቃለል በክልሉ ከሁሉም መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ሰዎችን በአባልነት ያቀፈ ግብረ ሃይል በማቋቋም ግብር በአግባቡ በማይከፍሉ ነጋዴዎች ላይ የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በክልሉ ለሶስት ሳምንታት በተካሄደ ሥርዓት የማሲያዝ እንቅስቀሴ ፈቃድ ሳይኖራቸውና ግብር ሳይከፈሉ ሲነግዱ የተገኙ 720  የንግድ ሱቆች በህግ አግባብነት እንዲታሸጉ መደረጉን አስረድተዋል።

ከመካከላቸውም 405 ንግድ ፈቃድ በማውጣት ወደ ግብረ ከፋይነት መምጣታቸውን ጠቅሰው፤ ቀሪዎቹም የጊዜ ገደብ ተሰጥቷቸው በተመሳሳይ ሥርዓት ለማሲያዝ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ግብረ ሃይሉ ባከናወነው ሥራ ከማስታወቂያ፣ መደብ፣ ከዓመታዊ የንግድ ትርፍና ሌሎችም የገቢ ምንጮች ሳይከፈል የቆየ ከ34 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ወይዘሮ ሠሚራ ጠቁመዋል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የንግድ ሱቃቸው የታሸገባቸው ነጋዴዎች የገቢዎች ቢሮ ግንዛቤ ለመፍጠር መስራት እንዳለበት ገልጸዋል።

ቢሮው በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሉበትን ክፍተቶች ማስተካከል እንዳለበት ጠቁመዋል።

ቅሬታ በማስተናገድ በኩል የጀመረውን ጥረት ሊያጠናክር እንደሚገባም አመልክተዋል።

ከ13ሺ በላይ ግብር ከፋዮች ያሉት የሐረሪ ክልል በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ ከቀጥተኛ፣ ቀጥተኛ ካልሆነ ታክስና ሌሎችም የገቢ ምንጮች ከ361 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱንና ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ77 ሚሊዮን 400ሺህ ብር ብልጫ እንዳለው ተገልጿል።