ኢትዮጵያ በ38ኛው የካርቱም ዓለምአቀፍ የንግድ አውደ ርዕይ እየተሳተፈች ነው

ኢትዮጵያ በ38ኛው የካርቱም ዓለምአቀፍ የንግድ አውደርዕይ እየተሳተፈች መሆኑ ተገለጸ፡፡

በካርቱም ለ8 ቀናት የሚቆየውን ዓለምአቀፍ የንግድ አውደርዕይ የሱዳን የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አምባሳደር ኦማር ማኔስ እና ሌሎችም የሱዳን መንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ከፍተዋል።

በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ የካርቱም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ኤምባሲ ምክትል የሚስዮን መሪ መኮንን ጎሳዬ፣ የሱዳን የካቢኔ ሚኒስትር አምባሳደር ኦማር ማኒስ፣ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር ዶክተር ሂባ መሃመድና የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መድኔ አባስ መድኔ በመገኘት የኢትዮጵያ ባህላዊ የቡና አፈላል ሥነ ሥርዓት ላይ ታድመዋል።

በኤግዚብሽኑ በሱዳን የሚገኙ የተለያዩ አገራት ኤምባሲዎች እንዲሁም ከተለያዩ አገራት የመጡ በርካታ ኩባንያዎች እየተሳተፉ ናቸው።

የኢትዮጵያ ኤምባሲም ሀገሪቱ ያሏትን የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም እድሎች እንዲሁም “Rising Ethiopia” በሚል የምታከናውናቸውን የልማት ሥራዎች ለአውደርዕዩ ታዳሚዎች በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል።

በአነስተኛና መካከለኛ ጀረጃ የሚገኙ በአልባሳት፣ በቆዳ ውጤቶች፣ ባህላዊ ምግቦችና አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በኮንስትራክሽን ግብአት ምርት ላይ የተሰማሩ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች የወጭ ምርቶቻቸውን ለኤግዝብሽኑ ጎብኚዎች በማስተዋወቅ ላይ እንደሆነም ነው የተገለጸው።

አውደርዕዩ ከአቻ ኩባንያዎች ጋር የንግድ ትስስር በመፍጠር ለምርቶቻቸው የገበያ እድል የሚያገኙበት እንደሚሆን ከውጭ ጉዳይ ቃልአቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።