የተለያዩ ቅርጽና መጠን ያላቸው 143 ሳተላይቶች በአንድ ሮኬት ተጭነው ከፍሎሪዳ ወደ ህዋ ተመንጥቀዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ በአንድ ሮኬት ብዙ ሳተላይት ተልኮ የነበረው በፈረንጆቹ 2017 ሲሆን የሳተላይቶቹ ብዛትም 104 ብቻ ነበር፡፡
ያን ጊዜ ሳተላይቶቹን ያሳፈረው መንኩራኮር ሕንድ ሠራሽ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
አሁን ክብረ ወሰኑን የሰበረው የዓለም ቁጥር 1 ቢሊየነር ኤለን መስክ ኩባንያ የፈጠረው ስፔስኤክስ- ፋልከን ነው፡፡
ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ሳተላይቶች በአንድ ጊዜ መላክ መቻሉ ቀስ በቀስ የአሠራርና የቴክኖሎጂ አብዮት እየተደረገ እንደሆነ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡
ይህም ማለት አንድን ሳተላይት በመጠኑ አሳንሶ፣ በሥራ ቅልጥፍና አዘምኖ በትንንሽ ግብአቶች አምርቶ ወደ ህዋ ማሳፈር መቻሉ ነው፡፡
አሁን አሁን ማንም ኩባንያ ልክ የእጅ ስልክ ማምረት እንደሚችለው ሳተላይቶችን ማምረት የሚችልበት አቅም መፈጠሩን ያስመሰከረ ነው ብለውታል ባለሙያዎች፡፡
አዲሱ የህዋ ታክሲ ስፔስኤክስ (SpaceX) እነዚህ ቀላል ሳተላይቶችን ወደ ኦርቢት ለመላክ ከ1 ሚሊዮን ዶላር ባነሰ ዋጋ መጠየቁ ወደፊት ዘርፉ ለትንንሽ ኩባንያዎች እየተከፈተ እንደሚመጣ አመላካች ነው ተብሏል፡፡
ስፔስኤክስ የራሱ የሆኑ 10 ሳተላይቶች ያሉት ሲሆን በዓለም ዙርያ ብሮድባንድ ኢንተርኔት ግንኙነቶችን መስጠት ይጀምራል ተብሏል፡፡
በዚህ ክብረ ወሰንን በሰበረው የሮኬት ጉዞ የሳንፍራንሲስኮው ፕላኔት የተባለ ኩባንያ 48 ሳተላይቶችን በመላክ ከፍተኛውን የሳተላይት ቁጥር አስመዝግቧል፡፡
እነዚህ የፕላኔት ኩባንያ ንብረት የሆኑ ሳተላይቶች ‹ሱፕርዶቭ› ሞዴል የሚባሉ ሲሆን የመሬትን ገጽታ በየቀኑ በከፍተኛ ጥራት ፎቶ የሚያነሱ ናቸው፡፡
አሁን የላካቸውን 48 ሳተላይቶች ጨምሮ ይህ የሳንፍራንሲስኮው ፕላኔት ኩባንያ በህዋ የሚኖሩት የሳተላይቶች ቁጥር ወደ 200 የሚያደርሰው ይሆናል፡፡
ሱፐርዶቭስ የሚባሉት እነዚህ ሳተላይቶች መጠናቸው የሊስትሮ ሳጥን ቢያክል ነው፡፡ ሌሎቹ በፋልከን ሮኬት የተጫኑት ደግሞ ከአንድ የሻይ ኩባያ መጠን ብዙም የሚበልጡ አይደሉም፡፡
አሁን አሁን ቴክኖሎጂው እየተረቃቀ ሲመጣ የሳተላይቶች ተግባር ሳይቀንስ፣ ነገር ግን መጠናቸው እጅግ እያነሰ ሄዶ ‹ስፔስቢስ› የሚባሉ ‹የህዋ-ንብ› ሊባሉ የሚችሉ ትንንሽ ሳተላይቶች እየተፈጠሩ ነው፡፡
የነዚህ ሳተላይቶች ጠቅላላ መጠን 10 ሴንቲ ሜትር በ10 ሴንቲሜትር ብቻ ቢሆን ነው፡፡
እነዚህ ‹ስፔስቢስ› የሚባሉት የሳተላይት ጉጦች ሳተላይትን መሬት ላይ ካለ ማንኛውም ቁስ ጋር የማገናኘት ተግባር ይሰጣሉ፡፡
(ምንጭ ፡- ቢቢሲ)