የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና የሳኒቴሽን መሰረተ ልማት ግንባታዎች አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሀብት መስኖ እና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን፣ የመስኖ ልማት ኮሚሽን እና የውሃ ልማት ኮሚሽን የ2013 ዓ.ም የ6 ወራት እቅድ አፈጻጸማቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሀብት መስኖ እና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርበዋል፡፡
በገጠርም ይሁን በከተማ በስፋት የሚስተዋለውን የውሃ ችግር ለማቃለል ይቻል ዘንድ የተቋቋመው የውሃ ልማት ኮሚሽን ችግሩን ለመቅረፍ የተለያዩ ስራዎችን ቢያከናውንም ኮሚሽኑ በስድስት ወራት ውስጥ የሰራቸው ስራዎች ከተቀመጠው እቅድ አንጻር ዝቅተኛ መሆኑ ለምክር ቤቱ ባቀረበው ሪፖርት ተመላክቷል፡፡
የውሃ ልማት ኮሚሽን በ13 ከተሞች የተቀናጀ የከተማ አቀፍ የሳኒቴሽን መሰረተ ልማት በ10 ከተሞች ለሚገነቡ የህዝብ እና የጋራ መጸዳጃ ቤቶች የኮንትራክተር ቅጥር መፈጸሙን እና በ5 ከተሞች ደግሞ የሳኒቴሽን መሰረተ ልማት ግንባታ ማከናወኑንም በሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡
በገጠር ያለውን የውሃ አቅርቦት ለማሻሻል የሚያግዙ የ41 ፕሮጀክቶች ግንባታ በእቅድ የተያዙ ሲሆን በሳኒቴሽን በኩልም አዲስ አበባን ጨምሮ በ22 የተለያዩ ከተሞች ችግሩን ለመቅረፍ ኮሚሽኑ ጥናት አካሂዷል፡፡
በኮሚሽኑ በኩል ያሉ የስራ አፈጻጸም ድክመቶችን በአስቸኳይ ተቀርፈው የተሻለ የውሃ አቅርቦት በገጠር እና ከተማ እንዲኖር እንደሚሰራም ነው ያስታወቀው፡፡
የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን ባቀረበው የአፈጻጸም ሪፖርት በ6 ወራት የተሻለ አፈጻጸም ያለው መሆኑ የተነሳ ሲሆን ባለስልጣኑ የቴሩ ጭፍራ እና ቆቦ ጨፉ የከርሰ ምድር ውሃ ጥናት ዲዛይን እና ግንባታ ስራ በ6 ወራት ትልቅ አፈፃፀም የታየባቸው ናቸው ተብሏል፡፡
የመስኖ ልማት ኮሚሽን በ6 ወራት እቅድ አፈጻጸሙ የጊዳቦ ግድብ እና መስኖ ልማት ፕሮጀክት፣ የእርሻ መሬት መለየት ስራ እና የመስኖ አውታሮች ጥገና ፕሮጀክት የተሻለ አፈጻጸም የታየባቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የመስኖ ልማት ኮሚሽን በአብዛኛው ዝቅተኛ አፈጻጸም እንደነበረው በውይይቱ ተገልጿል፡፡
ኮሚሽኑ አነስተኛ አፈጻጸም ያሳየበትን ዋነኛ ችግር በመለየት በትኩረት መስራት አለበትም ተብሏል፡፡
(በሜሮን መስፍን)