በምግብ ዘይት ላይ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰድ ተጀመረ

በዘይት ዋጋ ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አከበረኝ ውጋገን እንደገለጹት በቅርቡ በዘይት ዋጋ ላይ የተከሰተው የዋጋ ጭማሪ ምክንያታዊ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች የንግድ ተቋማት በተደረገ ድንገተኛ አሰሳ ከስምምነቱ ውጪ ሲሸጡ በመገኘታቸው ቢሮ ከንግድ ሚኒስቴር እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ዋጋን ለማረጋጋት በስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡

በስምምነቱም የዘይት ዋጋ ከሁለት ወራት በፊት ወደ ነበረበት የመሸጫ ዋጋ እንዲመለስ የጋራ መግባባት ላይ ቢደረስም በስምምነቱ መሰረት የዘይት ዋጋ ቅናሽ አለማሳየቱን የተቋቋመው ግብረሃይል በዳረገው ቅኝት ማረጋገጡን አቶ አከበረኝ አንስተዋል፡፡

በተቀመጠው የዋጋ ተመን መሰረት ባለ 5 ሊትሩን ዘይት ከ360 ብር በላይ በሚሸጡ ነጋዴዎች ላይ ቢሮው እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በ240 በሚደርሱ የንግድ ተቋማት ላይ በተደረገ ድንገተኛ አሰሳ 10 የሚሆኑት ከስምምነቱ ውጪ ሲሸጡ መገኘታቸውን የገለጹት አቶ አከበረኝ፣ እነዚህ ድርጅቶች ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው መሆኑን እና ከዛሬ ጀምሮም አምስት ሊትሩንን ዘይት 360 ብር በላይ በሚሸጡ ነጋዴዎች ላይ የማሸግ እርምጃ እንደሚወሰድ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡