ከኢንዱስትሪ ፓርኮች በ2013 በጀት ዓመት አጋማሽ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ተገኘ

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በ2013 በጀት አጋማሽ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማግኘቱን አስታወቀ።

በግማሽ ዓመቱ ከ19ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠሩንም ነው ገለጸው፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የ2013 በጀት አመት የመጀመሪያ 6 ወር የስራ ዕቅድ አፈፃፀሙን በድሬዳዋ ከተማ ገምግሟል፡፡

በዚህ ወቅት እንደተገለጸው በ2013 የበጀት ዓመት የመጀመሪያ 6 ወራት 83,972,421 የአሜሪካን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የተቻለ ሲሆን 548,036 የአሜሪካ ዶላር የሚሆነው የግል የአደጋ መከላከያ መሣሪያ ምርት ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከውጭ ሀገር ገበያ ተገዝተው ለሀገር ውስጥ ገበያ ሊቀርቡ ይችሉ የነበሩ ምርቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያሉ ድርጅቶች ማምረት እንዲችሉ በማድረግ 20,325,897 የአሜሪካን ዶላር የሚያወጣ ምርት ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ኮርፖሬሽኑ ገልጿል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሥራ የጀመሩ ሁሉም ኢንዱስትሪ ፓርኮች ማምረት ከጀመሩበት ግዜ አንስቶ እስከ አሁን 571,004,188 የአሜሪካን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ለውጭ ገበያ መቅረቡ ነው የተነገረው።

በግማሽ ዓመቱ ኮርፖሬሽኑ ለ19,757 ወጣቶች የስራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን በኮርፖሬሽኑ በአጠቃላይ የፋብሪካ ሰራተኞችን ጨምሮ ከ70 ሺህ በላይ ዜጎች ስራ ዕድል እንዲያገኙ መደረጉም ተነስቷል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ ኮርፖሬሽኑ ከተቋቋመበት ግዜ አንስቶ ባለፉት አምስት ዓመታት 13 ያህል ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማልማት 11 ያህሉን ወደ ምርት ሂደት ማስገባት ያስጀመረ ሲሆን የግል ኢንዱስትሪ ፓርክ አልሚዎችን በመደገፍ እየደገፈ እንደሚገኝ አስታውቋል።