በአንዳንድ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት መጓደል አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል- ኤጀንሲ

በአንዳንድ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት መጓደል አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

አንዳንድ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሕግ ውጭ በመንቀሳቀስ በትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደሩ ነው የተባለው፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርና የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትምህርት ጥራት ላይ ተወያይተዋል።

ተቋማቱ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ራሳቸውን እንዴት ማዘመን ይችላሉ፣ የጥናትና ምርምር ስራዎችንስ በምን መልኩ መስራት ይኖርባቸዋል የሚሉትና ሌሎችም በውይይቱ የተነሱ ጉዳዮች መሆናቸው ተጠቁሟል።

በውይይቱ እንደተመላከተው ተቋማቱ ባለፉት ዓመታት በቁጥር ደረጃ ቢጨምሩም፤ ጥራትና አግባብነት ላይ ውስንነት ይታይባቸዋል።

ከከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት አጀንሲ የተገኘው መረጃ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቁጥር 278 መድረሱን ያሳያል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዱዓለም አድማሴ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጠው ትምህርት የጥራት መጓደል አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ገልጸው፣ “አንዳንድ ተቋማት ከ10ኛ ክፍል ላቋረጡ ተማሪዎች ዲግሪ ይሰጣሉ፤ ማንበብና ማጻፍ የማይችሉ ሰዎችም እንዲሁ ወረቀት እየወሰዱ ነው” ብለዋል።
(ምንጭ፡-ኢዜአ)