ምርት ገበያ በጎንደር ከተማ ያቋቋመውን የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከል ሥራ አስጀመረ

 

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በጎንደር ከተማ ያቋቋመውን የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከል ሥራ አስጀመረ።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ 347 አባላትና ከ140 በላይ አባል ያልሆኑ ተገበያዮች እንዲሁም የኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከላት በአዲስ አበባ፣ በሃዋሳ፣ በሑመራና በነቀምት ከ22 ሺህ በላይ ደንበኞች አሉት።

ዛሬ ደግሞ በጎንደር ከተማ ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከልን ወደ ሥራ አስገብቷል። ማዕከሉ ከ90 በላይ ተገበያዮችን በአንድ የግብይት መርሐ ግብር ማስተናገድ የሚችል ነው።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የኢፌዴሪ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበልና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ነው ወደ ሥራ መግባቱ የተበሰረው።

የአካባቢው ተገበያዮች ወደ አዲስ አበባ መሔድ ሳይጠበቅባቸው በቀጥታ የግብይት ውድድሩ አካል እንዲሆኑ የሚያስችላቸው ዘመናዊ አሰራር ነው። ይህም ከፍተኛ ወጭንና እንግልትን የሚቀንስ አሰራር ነው ተብሏል።

ምርት ገበያው የጥራጥሬና ቅባት እህሎችንና ቡና አቅራቢዎች ከሸማቾች ጋር በኤሌክትሮኒክ ሥርዓት በመደራደር የሚገበያዩበት ዘመናዊና ቀልጣፋ አሠራር መሆኑን በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የንግድ ኦፕሬሽን ከፍተኛ ስፔሻሊስት አቶ ቸርነት ታመነ ለአብመድ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የጎንደር ኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከል ሲገበያዩ ያገኘናቸው ደንበኞች ከዚህ በፊት ሻጭና ገዥ አዲስ አበባ ድረስ በመሔድ ለከፍተኛ ወጭና እንግልት ይዳረጉ እንደነበር ነግረውናል።

አሁን ላይ በአቅራቢያቸው የኤሌክትሮክ ግብይት ማዕከል መገንባቱ ወጭን በመቀነስ ፍትሐዊና ቀልጣፋ ግብይት እንድንፈጽም ያስችለናል ብለዋል ተገበያዮቹ።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በአንድ ጊዜ 400 ሺህ ሜትሪክ ቶን የሚይዙ ከ60 በላይ መጋዘኖችና 23 ቅርንጫፎች አሉት። ከሦስት ሚሊየን በላይ አርሶ አደሮችም በቀጥታና በተዘዋዋሪ ይጠቀማሉ።

12 የግብርና ምርቶችን ያገበያያል፤ ከ17 ባንኮች ጋር በአጋርነት ይሠራል። በዓመት ከ700 ሺህ ቶን በላይ ምርት የሚያገበያይ ሲሆን በዓመት ከ33 ቢሊየን ብር በላይ ክፍያና ርክክብ ይፈፅማል።
(ምንጭ፡- አብመድ)