የጨጎማ-ጋሸና መንገድ ግንባታ መጀመር የረጅም ጊዜ ጥያቄያችንን መልሷል – ነዋሪዎች

የጨጎማ-ጋሸና መንገድ ግንባታ መጀመር የረጅም ጊዜ የመሰረተ ልማት ጥያቄያቸውን የመለሰ መሆኑን በአማራ ክልል ዋድላ ወረዳ የኮን ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ግንባታው ባለፈው ሳምንት በይፋ የተጀመረውን የጨጎማ-ጋሸና መንገድ ግንባታን አስመልክቶ ኢዜአ የአካባቢውን ነዋሪዎች አነጋግሯል።

በዋድላ ወረዳ ኮን ከተማ በንግድ ሥራ ተሰማርተው ለ20 ዓመታት መኖራቸውን የገለጹት አቶ ወርቅዬ ገቤ “ህብረተሰቡ ስብሰባ በተካሄደ ቁጥር የመንገድ ይሰራልን ጥያቄውን ደጋግሞ ሲያነሳ ነበር” ይላሉ።

በመንገድ እጦት በአካባቢው በስፋት የሚመረቱ የግብርና ውጤቶችን ወደ መሀል ከተማ ለመላክ አስቸጋሪ እንደነበረም አውስተዋል።

ምላሽ ያገኘው የመንገዱ ግንባታ ጥያቄ ለውጤት እስኪበቃ ከተቋራጮችና ከአመራሩ ጋር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

በዋድላ ወረዳ ተወልዶ ያደገው ወጣት ጀማል ፈለቀ የመንገዱ መገንባት በክረምት ወቅት የሚያጋጥማቸውን ችግር እንደሚፈታ ገልጾ፤ “ኅብረተሰቡ መንገዱን በእኔነት ስሜት የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት” ብሏል።

በአካባቢው ለረጅም ጊዜ በትራንስፖርት ዘርፍ የሰሩት ወጣት ይኸው ሀብታሙ እና ወጣት ብርሃነመስቀል አበረ በበኩላቸው የመንገዱ መሰራት በመንገዱ አስቸጋሪነት የተነሳ የትራንስፖርት አገልግሎት ማግኘት ፈታኝ እንደሆነ አስታውሰዋል።

የተሽከርካሪ ባለንብረቶች መኪናቸው እንዳይጎዳ ወደአካባቢው መምጣት እንደማይፈልጉ አንስተው፤ የመንገዱ መገንባት ለኅብረተሰቡ፣ ለአሽከርካሪዎችና ለባለንብረቶች ምቹ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ መንገዱ በወቅቱ ባለመጀመሩ በአካባቢው ኅብረተሰብ ዘንድ ቅሬታ ፈጥሮ እንደነበረ አስታውሰዋል።

መንግስት የሕዝቡን የልማት ጥያቄና ፍላጎት እየመለሰ መሆኑን ጠቅሰው፤ “ቃል በተገባው መሰረት በአካባቢው በተደጋጋሚ የሚነሳውን የጨጎማ-ጋሸና መንገድ ግንባታ አስጀምሯል” ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የአካባቢው ነዋሪዎች የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።