የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች በጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ የሚመራውን መንግስት በመደገፍ ሠላማዊ ሠልፍ አካሄዱ

የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የሚመራውን መንግስት እንደሚደግፉ ዛሬ ባካሄዱት ሠላማዊ ሠልፍ ገለጹ።

በሠልፉ ብዛት ያላቸው የአሶሳ እና አካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

በድጋፍ ሠልፉ ከተሳተፉ መካከል አቶ የሱፍ ከበደ በአገሪቱ ህዝቦች መካከል የተዘራው ጥርጣሬ ከመቀራረብ ይልቅ በስጋት እንዲተያዩ ማድረጉን ገልጸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ይህንን በመለውጥ መሻሻል እንዲመጣ ማድረጋቸውን አውስተዋል፡፡

በቀጣይም እሳቸው በሚመሩት መንግስት ኢትዮጵያ የተሻለ ደረጃ ላይ እንደምትደርስ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

“ዶክተር ዐቢይን ለመደገፍ የተነሳሳሁት የአገር አንድት እንዲጠናከር በፈጸሙት ተግባር ነው” ያሉት ደግሞ ሌላዋ የሠልፉ ተሳታፊ ወይዘሮ ከሪማ ሳህሊ ሲሆኑ፣ “ብሔር ብሔረሰቦችን ያለልዩነት መርተዋል፤ የሴቶች ተሳትፎ እንደሚጨምር አድርገዋል” ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በተለይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝብ ከሌላው ወንድም ኢትዮጵያዊያን ጋር በእኩልነት ጎልቶ እንዲወጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል፡፡

የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት በስኬት የተከናወነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር በቅርቡ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኡመር መሃመድ መንግስት በአገሪቱ እውነተኛ ፌደራሊዝም በማስፈን ወደ ብልጽግና ለመውሰድ እየተጋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህን ለማስተጓጎል የሚጥሩ ሃይሎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ “የመንግስት ጥረት እንዲሳካ ከጎናችን የቆመው ህዝብ ድጋፉ እንደሚቀጥል አልጠራጠርም” ብለዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኢስሃቅ አብዱልቃድር በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሳል አመራር አገሪቱ ወደ ለውጥ እየተጓዘች መሆኗን ተናግረዋል፡፡

“ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጤት ያስመዘገቡት የአገር ውስጥ እና የዓለም ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁመው ነው” ያሉት ሃላፊው፤ የህዝቡ ድጋፍ ወቅታዊ እና ለበለጠ ስራ እንደሚያተጋ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡